የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍል 15:22-41

ዘኍል 15:22-41 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ ‘እንግዲህ ካለማወቅ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ከሰጣቸው ትእዛዞች አንዱን ሳትፈጽሙ ብትቀሩ፣ ይህም ማለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዞቹን ከሰጠበት ዕለት ጀምሮ በተከታታይ ትውልዶች በሙሴ አማካይነት ያዘዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ባታደርጉ፣ ይህም የተፈጸመው ሆን ተብሎ ሳይሆንና ማኅበረ ሰቡም ሳያውቀው ከሆነ፣ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ አድርጎ አንድ ወይፈን በእሳት ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚሁም ጋር ሥርዐቱ የሚጠይቀውን የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ደግሞም ለኀጢአት መሥዋዕት ተባዕት ፍየል ያቅርብ። ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ፤ ምክንያቱም ባለማወቅ የተፈጸመ ስለ ሆነና ስለ ስሕተታቸውም በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) ስላቀረቡ ነው። ባለማወቅ የተደረገውን ስሕተት ሁሉም የፈጸሙት ስለሆነ፣ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብና በመካከላቸው የሚኖር መጻተኛ ሁሉ ይቅር ይባላል። “ ‘ነገር ግን አንድ ሰው ካለማወቅ የተነሣ በግሉ ኀጢአት ቢሠራ ግን ለኀጢአት መሥዋዕት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያምጣ። ከዚያም ካህኑ፣ ባለማወቅ ኀጢአት ሠርቶ ለተሳሳተው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ስርየት በሚደረግለትም ጊዜ ሰውየው ይቅር ይባላል። ያገር ተወላጅ እስራኤላዊ ይሁን ወይም መጻተኛ ባለማወቅ ኀጢአት ከሠራ በማናቸውም ሰው ላይ ሕጉ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል። “ ‘ያገር ተወላጅም ይሁን መጻተኛ ሆን ብሎ ኀጢአት የሚሠራ ማንኛውም ሰው ግን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ስለሚያቃልል ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ስለናቀ፣ ትእዛዞቹንም ስለ ጣሰ ያ ሰው በርግጥ ተለይቶ መጥፋት አለበት፤ ጥፋቱ የራሱ ነው።’ ” እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ አንድ ሰው በሰንበት ቀን ዕንጨት ሲለቅም ተገኘ። ዕንጨት ሲለቅም ያገኙትም ሰዎች ሰውየውን ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው የእስራኤል ማኅበር አመጡት፤ በሰውየው ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ የሆነ ነገር ባለመኖሩ በጥበቃ ሥር እንዲቈይ አደረጉት። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ሰውየው ይሙት፤ መላውም ማኅበር ከሰፈር ውጭ በድንጋይ ይውገረው” አለው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ማኅበሩ ሰውየውን ከሰፈር አውጥቶ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገረው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ በየልብሳችሁ ጫፍ ላይ ዘርፍ አድርጉ፤ እያንዳንዱም ዘርፍ ሰማያዊ ጥለት ይኑረው። ልባችሁ የተመኘውን፣ ዐይናችሁ ያየውን ሁሉ ተከትላችሁ እንዳታመነዝሩ እነዚህን ዘርፎች በማየት የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዞች በማስታወስ እንድትታዘዙ ማስታወሻ ይሆኗችኋል። ስለዚህ ትእዛዞቼን ሁሉ ለመፈጸም ታስባላችሁ፤ ለአምላካችሁም (ኤሎሂም) የተቀደሳችሁ ትሆናላችሁ። አምላካችሁ (ኤሎሂም) እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነኝ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”

ዘኍል 15:22-41 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ብት​በ​ድ​ሉም፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሙሴ ያዘ​ዛ​ቸ​ውን እነ​ዚ​ህን ትእ​ዛ​ዛት ሁሉ ባታ​ደ​ርጉ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ካዘ​ዘ​በት ከፊ​ተ​ኛው ቀን ጀምሮ ወደ ፊትም እስከ ልጅ ልጃ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሙሴ እጅ እንደ አዘ​ዛ​ችሁ ባታ​ደ​ርጉ፥ በማ​ኅ​በ​ሩም ፊት ያል​ታ​ወቀ ኀጢ​አት ቢኖር፥ ማኅ​በሩ ሁሉ ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕ​ትና ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጎ መዓዛ እን​ዲ​ሆን ከመ​ን​ጋ​ዎች አንድ ንጹሕ ወይ​ፈን ያቀ​ር​ባሉ። የእ​ህሉ ቍር​ባ​ንና የመ​ጠጡ ቍር​ባ​ንም እንደ ሕጉ ነው፤ ለኀ​ጢ​አ​ትም መሥ​ዋ​ዕት አንድ አውራ ፍየል ያቀ​ር​ባሉ። ካህ​ኑም ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ማኅ​በር ሁሉ ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ላ​ቸ​ዋል፤ ባለ​ማ​ወቅ ነበ​ርና ይሰ​ረ​ይ​ላ​ቸ​ዋል፤ እነ​ር​ሱም ስለ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ውና ስላ​ለ​ማ​ወ​ቃ​ቸው ቍር​ባ​ና​ቸ​ው​ንና መሥ​ዋ​ዕ​ታ​ቸ​ውን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያቀ​ር​ባሉ። በሕ​ዝ​ቡም ሁሉ ዘንድ ያለ ዕው​ቀት ተደ​ር​ጎ​አ​ልና ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ማኅ​በር ሁሉ ወደ እና​ን​ተም ለሚ​መጣ መጻ​ተኛ ስር​የት ይደ​ረ​ግ​ላ​ቸ​ዋል። “አንድ ሰው ሳያ​ውቅ ኀጢ​አት ቢሠራ፥ ስለ ኀጢ​አት አን​ዲት የአ​ንድ ዓመት እን​ስት ፍየል ያቀ​ር​ባል። ካህ​ኑም ባለ​ማ​ወቅ ስለ በደ​ለው ያስ​ተ​ሰ​ር​ያል፤ ባለ​ማ​ወ​ቅም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ኀጢ​አት ስለ ሠራው ሰው ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል። ትው​ልዱ በእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች መካ​ከል ቢሆን፥ ወይም በመ​ካ​ከ​ላ​ቸው የሚ​ኖር መጻ​ተኛ ቢሆን፥ ሳያ​ውቅ ኀጢ​አ​ትን ለሚ​ሠራ ሁሉ ሕጉ አንድ ይሆ​ን​ለ​ታል። የሀ​ገር ልጅ ቢሆ​ንም ወይም መጻ​ተኛ ቢሆን፥ በእጁ ትዕ​ቢ​ትን የሚ​ያ​ደ​ርግ ሰው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሰድ​ቦ​አል፤ ያም ሰው ከሕ​ዝቡ መካ​ከል ተለ​ይቶ ይጠ​ፋል። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ስለ​ናቀ፥ ትእ​ዛ​ዙ​ንም ስለ ሰበረ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኀጢ​አቱ በራሱ ላይ ነው።” የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች በም​ድረ በዳ ነበሩ፤ አንድ ሰውም በሰ​ን​በት ቀን ዕን​ጨት ሲለ​ቅም አገኙ። በሰ​ን​በት ቀን ዕን​ጨት ሲለ​ቅም ያገ​ኙ​ትም ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን፥ ወደ እስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ማኅ​በር ሁሉ አመ​ጡት። እን​ዴት እን​ደ​ሚ​ያ​ደ​ር​ጉት አል​ፈ​ረ​ዱ​ምና በግ​ዞት ቤት አዋ​ሉት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን እን​ዲህ ብሎ ነገ​ረው፥ “ሰው​ዬው ይገ​ደል፤ ማኅ​በ​ሩም ሁሉ በድ​ን​ጋይ ይው​ገ​ሩት” አለው። ማኅ​በ​ሩም ሁሉ ከሰ​ፈሩ ወደ ውጭ አወ​ጡት፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን እን​ዳ​ዘ​ዘው በድ​ን​ጋይ ወገ​ሩት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን እን​ዲህ ብሎ ተና​ገ​ረው፦ “ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች እን​ዲህ በላ​ቸው፦ እነ​ር​ሱም በት​ው​ል​ዳ​ቸው ሁሉ በል​ብ​ሳ​ቸው ጫፍ ዘርፍ ያደ​ርጉ ዘንድ፥ በዘ​ር​ፉም ሁሉ ላይ ሰማ​ያዊ ፈትል ያደ​ርጉ ዘንድ እዘ​ዛ​ቸው። እር​ሱም በዘ​ርፉ ይሁ​ን​ላ​ችሁ፤ ትመ​ለ​ከ​ቱ​ታ​ላ​ች​ሁም፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ትእ​ዛ​ዛት ታስ​ባ​ላ​ችሁ፤ ታደ​ር​ጉ​አ​ቸ​ው​ማ​ላ​ችሁ፤ እነ​ር​ሱን በመ​ከ​ተል ያመ​ነ​ዘ​ራ​ች​ሁ​ባ​ትን የሕ​ሊ​ና​ች​ሁ​ንና የዐ​ይ​ኖ​ቻ​ች​ሁን ፈቃድ አት​ከ​ተሉ። ትእ​ዛ​ዙን ታስ​ቡና ታደ​ርጉ ዘንድ፥ ለአ​ም​ላ​ካ​ች​ሁም ቅዱ​ሳን ትሆኑ ዘንድ፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝ፤ አም​ላክ እሆ​ና​ችሁ ዘንድ ከግ​ብፅ ምድር ያወ​ጣ​ኋ​ችሁ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝ።”

ዘኍል 15:22-41 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ብትስቱም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ እግዚአብሔር ካዘዘበት ከፊተኛው ቀን ጀምሮ ወደ ፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥ ማኅበሩ ሳያውቁ በስሕተት ቢደረግ፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋር እንደ ሕጉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቀርባሉ። ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ስሕተትም ነበረና ይሰረይላቸዋል፤ ስል ስሕተታቸውም ለእግዚአብሔር ቍርባናቸውን በእሳት አቅርበዋል፥ ለእግዚአብሔርም የኃጢአታቸውን መሥዋዕት አቅርበዋል። በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ ያለ እውቀት ተደርጎአልና ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል። አንድ ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል። ኃጢአት ሠርቶ ሳያውቅ፥ ለሳተ ለዚያ ሰው ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ይሰረይለትማል። ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ሳያውቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ ሕጉ አንድ ይሆንለታል። የአገር ልጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ አንዳች በትዕቢት የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስለ ሰበረ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኃጢአቱ በራሱ ላይ ነው። የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ። እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት። ያደርጉበትም ዘንድ የሚገባው አልተገለጠምና በግዞት አስቀመጡት። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት አለው። ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አውጡት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገሩት። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው። የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥ ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

ዘኍል 15:22-41 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“ምናልባት እናንተ ሆን ብላችሁ ሳይሆን ባለማወቅ እግዚአብሔር ለሙሴ ከሰጠው ትእዛዞች መካከል አንዱን ሳትጠብቁ ብትቀሩ፥ ወይም ምናልባት ወደፊት ዘሮቻችሁ በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ትእዛዝ ሁሉ ሳይፈጽሙ ቢቀሩ፥ እንዲህ ዐይነቱ ስሕተት የተፈጸመው በማኅበሩ አለማወቅ ከሆነ አንድ ወይፈን አምጥተው መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡት፤ ከእርሱም ጋር ተገቢውን የእህልና የወይን ጠጅ ቊርባን ያቅርቡ፤ በተጨማሪም አንድ ተባዕት ፍየል ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡ። ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ያስተስርይላቸው፤ ስሕተቱን የፈጸሙት ባለማወቅ ስለ ሆነና ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሆነውንም መሥዋዕትና የእህል ቊርባን አድርገው ለእግዚአብሔር ስላቀረቡ፥ ኃጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል። ሁሉም በአንድነት የስሕተቱ ተካፋዮች ስለ ሆኑ መላው የእስራኤል ማኅበርና በእነርሱም መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ኃጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል። “አንድ ሰው በግሉ ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ አንድ ዓመት የሞላት እንስት ፍየል ስለ ኃጢአቱ ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። ካህኑ በስሕተት ኃጢአት ለሠራው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተስርይለት፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል። የአገር ተወላጅ እስራኤላዊም ሆነ ወይም በዚያ የሚኖር መጻተኛ ባለማወቅ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ የሚከተለው ሕግ ይኸው ነው። “ነገር ግን የአገሩ ተወላጅም ሆነ መጻተኛ፥ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ የንቀት ዝንባሌ በማሳየቱ ከሕዝቡ ይለይ፤ ይህም የሚደርስበት እግዚአብሔር የተናገረውን ችላ ስላለና ከትእዛዞቹም አንዱን ሆን ብሎ ስለ ጣሰ ነው፤ ስለዚህ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኀላፊነቱ የራሱ ነው።” እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ጊዜ አንድ ሰው በሰንበት ቀን የማገዶ እንጨት ሲለቅም ተያዘ፤ የያዙትም ሰዎች መላው ማኅበር ወዳለበት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወሰዱት። በእርሱ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግልጥ ሆኖ ስላልተገኘ ለጊዜው በዘብ ተጠብቆ እንዲቈይ ተደረገ፤ ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “ሰውየው መገደል አለበት፤ መላው ማኅበር ከሰፈር አውጥተው በድንጋይ ወግረው ይግደሉት” አለው። ስለዚህ መላው ማኅበር ከሰፈር አውጥተው እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በድንጋይ ወግረው ገደሉት። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በልብሶቻችሁ ጫፍ ላይ ሁሉ ዘርፍ አብጁ፤ እያንዳንዱም ዘርፍ ከሰማያዊ ፈትል የተሠራ ጥለት ይኑረው፤ ይህንንም ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ አድርጉ፤ ዘርፎቹም እንደማስታወሻ ሆነው ስለሚያገለግሉ፥ እነርሱን በምታዩበት ጊዜ ሁሉ ትእዛዞቼን በማስታወስ ትፈጽማላችሁ፤ ከእኔም ርቃችሁ የገዛ ፈቃዳችሁንና ምኞታችሁን የምትፈጽሙ አትሆኑም፤ በልብሶቻችሁም ጫፍ ላይ የሚታዩት ዘርፎች ትእዛዞቼን ሁሉ እንድትፈጽሙ ያስታውሱአችኋል፤ እናንተም በፍጹም ለእኔ የተገዛችሁ ትሆናላችሁ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ፥ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”

ዘኍል 15:22-41 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“ነገር ግን ስሕተት ባለማወቅ ብትፈጽሙ፥ ጌታም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ጌታ ትዕዛዝን ከሰጠበት ቀን ጀምሮ ወደፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ ጌታ በሙሴ አንደበት ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥ ይህንንም ነገር ማኅበሩ ሳያውቀው በስሕተት የተደረገ ቢሆን፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቁርባንና ከመጠጡ ቁርባን ጋር እንደ ሕጉ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ባለማወቅ ስሕተት ፈጽመው ነበርና፥ ባለማወቅም ስለ ፈጸሙት ስሕተታቸው ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባናቸውን አምጥተዋልና፥ ማለማወቅም ስለ ፈጸሙት ስሕተታቸው የኃጢአታቸውን መሥዋዕት በጌታ ፊት አቅርበዋልና እነርሱ ይቅር ይባላሉ። ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ፥ ሕዝቡም ሁሉ ባለማወቅ ይህ ስሕተት ፈጽመዋልና በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል። “አንድ ሰው ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል። ባለማወቅም ኃጢአት ሠርቶ ስሕተትን ለፈጸመው ለዚያ ሰው እንዲያስተሰርይለት፥ ካህኑ በጌታ ፊት ማስተስሪያ ያደርጋል፤ እርሱም ይቅር ይባላል። ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ባለማወቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ። ነገር ግን የአገሩ ተወላጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ በትዕቢት ማናቸውንም ነገሮች የሚያደርግ ሰው ጌታን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። የጌታን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስላፈረሰ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ በደሉ በራሱ ላይ ነው።” የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ። እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት። በእርሱም ላይ ምን ሊደረግበት እንደሚገባ ገና ግልጽ አልነበረምና በእስር ቤት አኖሩት። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት።” ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አውጡት፥ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ እንዲያደርጉ፥ በዘርፉም ጫፍ ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል እንዲያኖሩበት እዘዛቸው። ዘርፉንም በልብሳችሁ ላይ አኑሩት እርሱንም በተመለከታችሁ ጊዜ የጌታን ትእዛዝ ሁሉ ታስታውሳላችሁ ታደርጉታላችሁም፥ ምኞታችሁንም በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዐይኖቻችሁን ፈቃድ የማትከተሉ ትሆናላችሁ። ስለዚህ ትእዛዜን ሁሉ አስታውሱት አድርጉትም፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ሁኑ። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”