ነህምያ 2:1-4
ነህምያ 2:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በንጉሡ በአርተሰስታ በሃያኛው ዓመተ መንግሥት በኔሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ ነበር፤ ጠጁንም አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። በፊቱም ሌላ ሰው አልነበረም። ንጉሡም፥ “ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኀዘን ነው እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ። ንጉሡንም፥ “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር፤ የአባቶች መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አያዝን?” አልሁት። ንጉሡም፥ “ምን ትለምነኛለህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።
ነህምያ 2:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር የወይን ጠጅ በመጣለት ጊዜ፣ የወይን ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ በፊቱ ዐዝኜ አላውቅም ነበር፤ ስለዚህ ንጉሡ፣ “ሳትታመም ፊትህ ለምን እንዲህ ዐዘነ? መቼም ይህ የልብ ሐዘን እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ። እኔም በጣም ፈርቼ ነበር፤ ለንጉሡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር፤ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ስትፈርስ፣ በሮቿም በእሳት ሲቃጠሉ ለምን ፊቴ አይዘን?” አልሁት። ንጉሡም፣ “ታዲያ ምን ትፈልጋለህ?” አለኝ። ከዚያም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ፤
ነህምያ 2:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር። ንጉሡም፦ “ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኅዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም” አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ። ንጉሡንም፦ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ! የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን?” አልሁት። ንጉሡም፦ “ምን ትለምነኛለህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።
ነህምያ 2:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አርጤክስስ በነገሠ በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር ከዕለታት በአንዱ ቀን ለንጉሠ ነገሥቱ የወይን ጠጅ አቀረብኩለት፤ ከዚያች ቀን በቀር ከዚህ ቀደም በፊቴ ላይ ምንም ዐይነት የሐዘን ምልክት አይቶብኝ አያውቅም ነበር። ስለዚህም “አንዳች የልብ ሐዘን ቢደርስብህ ነው እንጂ ሳትታመም እንዴት ይህን ያኽል በፊትህ የሐዘን ምልክት ይታያል?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም እጅግ በመፍራት፥ “ንጉሠ ነገሥቱ ለዘለዓለም ይኑር! የቀድሞ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፍርስራሽ ሆና ስትቀርና የቅጽሮችዋም በሮች በእሳት ሲወድሙ እንዴት አላዝንም?” ስል መለስኩለት። ንጉሠ ነገሥቱም “ታዲያ፥ አሁን የምትፈልገው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ፤ እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ከጸለይሁ በኋላ፥
ነህምያ 2:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሆነ በንጉሡ አርታሕሻስት በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር፥ የወይን ጠጅ በፊቱ ነበረ፥ የወይን ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ከዚህ ቀደም በፊቱ አዝኜ አላውቅም። ንጉሡም፦ “አልታመምክም ታዲያ ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኃዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም” አለኝ። እኔም እጅግ በጣም ፈራሁ። ንጉሡንም እንዲህ አልሁት፦ “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር! የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ስትፈርስ፥ በሮችዋም በእሳት ሲቃጠሉ ፊቴ ለምን አያዝን?” ንጉሡም፦ “ምን ትፈልጋልህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።