የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 9:2-32

ማርቆስ 9:2-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረዥም ተራራ ይዟቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም ዐጣቢ ዐጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋራ ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም ዐብሯቸው አልነበረም። ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ነበረበት ይመልሳል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል።” ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከብበዋቸው፣ የኦሪት ሕግ መምህራን ከእነርሱ ጋራ ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋራ የምትከራከሩት ስለ ምን ጕዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት።” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ በእግሮቹ ቆመ። ወደ ቤት ከገባም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ቀርበው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የዚህ ዐይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው። ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል ዐለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ማርቆስ 9:2-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን “መምህር ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። ቃሉንም ይዘው “ከሙታን መነሣት ምንድር ነው?” እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። እነርሱም “ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም መልሶ “ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፤ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት፤” አላቸው። ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ። ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፤ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። ጻፎችንም “ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ከሕዝቡ አንዱ መልሶ “መምህር ሆይ! ድዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፤ አልቻሉምም” አለው። እርሱም መልሶ “የማታምን ትውልድ ሆይ! እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት፤” አላቸው። ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። አባቱንም “ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኀም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን፤ እርዳንም፤” አለው። ኢየሱስም “ቢቻልህ ትላለህ? ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፤” አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ “አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው፤” አለ። ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና “አንተ ድዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፤ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም አትግባበት፤” አለው። ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም “ሞተ” እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ቆመም። ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ “እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው?” ብለው ብቻውን ጠየቁት። “ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም፤” አላቸው። ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤ ለእነርሱም “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፤ ይገድሉትማል፤ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል፤” ይላቸው ነበር። እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ማርቆስ 9:2-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረዥም ተራራ ይዟቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም ዐጣቢ ዐጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋራ ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም ዐብሯቸው አልነበረም። ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ነበረበት ይመልሳል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል።” ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከብበዋቸው፣ የኦሪት ሕግ መምህራን ከእነርሱ ጋራ ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋራ የምትከራከሩት ስለ ምን ጕዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት።” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ በእግሮቹ ቆመ። ወደ ቤት ከገባም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ቀርበው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የዚህ ዐይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው። ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል ዐለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ማርቆስ 9:2-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። ቃሉንም ይዘው፦ ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። እነርሱም፦ ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። እርሱም መልሶ፦ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፥ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት አላቸው። ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ። ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፥ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። ጻፎችንም፦ ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ከሕዝቡ አንዱ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው። እርሱም መልሶ፦ የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። አባቱንም፦ ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና፦ አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው። ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም፦ ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም። ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት። ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው። ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤ ለእነርሱም፦ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል ይላቸው ነበር። እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፥ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ማርቆስ 9:2-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ ወደ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ፤ በፊታቸውም መልኩ ተለወጠ። ልብሱ እጅግ አንጸባረቀ፤ በዓለም ላይ ማንም አጣቢ ያን ያኽል ሊያነጣ እስከማይችል ድረስ ነጭ ሆነ። በዚያን ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ተገልጠው ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! እዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እጅግ ደንግጠው ስለ ነበር ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፦ “የምወደው ልጄ ይህ ነው! እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ ተሰማ ወዲያውም ዞር ብለው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል አዘዛቸው። ቃሉንም ሰምተው በልባቸው ያዙት፤ ይሁን እንጂ “ይህ ከሞት መነሣት ምን ማለት ይሆን?” እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። እነርሱም፦ “የሕግ መምህራን መጀመሪያ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ስለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ይሁን እንጂ፥ የሰው ልጅ ከባድ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚናቅ የተጻፈው እንዴት ነው? እኔ ግን ኤልያስ ቀደም ብሎ መጥቶአል፤ ሰዎችም ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል” እላችኋለሁ። ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው በመጡ ጊዜ ብዙ ሰዎች በዙሪያቸው ተሰብስበው አዩ፤ የሕግ መምህራንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይከራከሩ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ኢየሱስን ባዩት ጊዜ በመገረም ተደናገጡ፤ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። ኢየሱስም “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት በምን ጉዳይ ነበር?” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡም መካከል አንዱ፥ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መምህር ሆይ፥ ድዳ በሚያደርግ መንፈስ የተያዘውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በሚነሣበትም ጊዜ ይጥለዋል፤ አፉም ዐረፋ እየደፈቀ ጥርሶቹን ያፋጫል፤ ሰውነቱም ደርቆ እንደ በድን ይሆናል፤ ርኩሱንም መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታምኑ ሰዎች! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” እነርሱም ልጁን ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩሱም መንፈስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ ወዲያው ልጁን ጥሎ አንፈራገጠው፤ ልጁም በመሬት ላይ እየተንከባለለ ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያኽል ጊዜ ነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለ፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው። ሊገድለውም እየፈለገ ብዙ ጊዜ በእሳትና በውሃ ውስጥ ይጥለዋል፤ ግን አንዳች ነገር ማድረግ ብትችል እባክህ እዘንልን! እርዳንም!” ኢየሱስም “ብትችል” ትላለህን? “ለሚያምን ሰው ሁሉ ነገር ይቻላል!” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “ማመንስ አምናለሁ፤ ግን ማመን በሚያቅተኝ ነገር ሁሉ ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ እየተራወጡ ሲመጡ አየ፤ ርኩሱንም መንፈስ “አንተ ድዳና ደንቆሮ መንፈስ ከልጁ እንድትወጣ ወደ እርሱም ተመልሰህ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ልጁንም በጣም ካንፈራገጠው በኋላ ወጣ፤ ልጁም ልክ እንደ በድን በመሆኑ ብዙዎቹ የሞተ መሰላቸው። ኢየሱስ ግን የልጁን እጅ ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ለመሆኑ ይህን ርኩስ መንፈስ እኛ ልናስወጣው ስለምን አልቻልንም?” ብለው ለብቻው ጠየቁት። እርሱም “እንዲህ ዐይነቱ በጸሎትና [በጾም] ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም አይወጣም።” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያንን ስፍራ ትተው በገሊላ በኩል ሄዱ፤ ያለበትን ቦታም ማንም ሰው እንዲያውቅ ኢየሱስ አልፈለገም፤ ይህም የሆነው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከተገደለ በኋላ ግን በሦስተኛው ቀን ይነሣል።” እያለ ያስተምራቸው ስለ ነበር ነው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህ ነገር አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ማርቆስ 9:2-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ይዟአቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፥ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፥ “ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም። ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፥ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፥ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም፥ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም፥ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ነገር እንደ ነበረ ያደርጋል፤ ታዲያ፥ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ያሻቸውን ሁሉ አድርገውበታል።” ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፥ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው፥ ጸሐፍት ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፥ “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት ስለምን ጉዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ አድሮበት ዲዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፏጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፥ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም አረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፥ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፥ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “አምናለሁ፤ አለማመኔን አይተህ እርዳኝ” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣታቸውን ባየ ጊዜ፥ “አንተ ደንቆሮና ዲዳ መንፈስ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዤሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎች “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው፥ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፥ “የዚህ ዓይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው። ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፥ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።