ማርቆስ 6:14-29
ማርቆስ 6:14-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል፤ ስለዚህም ኀይል በእርሱ ይደረጋል፤” አለ። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” አሉ፤ ሌሎችም “ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው፤” አሉ። ሄሮድስ ግን ሰምቶ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን “የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም፤” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር፤ አልቻለችም፤ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን “የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ፤ እሰጥሽማለሁ፤” አላት፤ “የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ፤” ብሎ ማለላት። ወጥታም ለእናትዋ “ምን ልለምነው?” አለች። እርስዋም “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለች። ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ፤” ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፤ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፤ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ፤ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።
ማርቆስ 6:14-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፣ “የዚህ ዐይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፣ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፣ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፣ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷል!” አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፣ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፣ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ ዐዘነ፤ በተጋበዙት እንግዶች ፊት የመሐላ ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ስለዚህ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፣ የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቈረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት።
ማርቆስ 6:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። ሌሎችም፦ ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም፦ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን፦ የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። ወጥታም ለእናትዋ፦ ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች። ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።
ማርቆስ 6:14-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የኢየሱስ ዝና በሁሉም ዘንድ ስለ ታወቀ፥ ንጉሡ ሄሮድስ ስለ እርሱ ሰማ። አንዳንድ ሰዎች፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል፤ ስለዚህ ይህ ሁሉ ተአምራት በእርሱ ይደረጋል” ይሉ ነበር። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” ይሉ ነበር፤ የቀሩትም ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት እንደ አንዱ ነው፤” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ግን ይህን ሁሉ ሰምቶ፦ “ይህ እኔ አንገቱን ያስቈረጥኩት ዮሐንስ ነው፤ እነሆ! እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮዲያዳን ስለአገባ ዮሐንስን በእርስዋ ምክንያት አስይዞ በወህኒ ቤት አስሮት ነበር። ዮሐንስም የታሰረው፥ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት ማግባትህ ተገቢ አይደለም!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ሄሮዲያዳ በዚህ ተቀይማ ዮሐንስን ልታስገድለው ትፈልግ ነበር፤ ነገር ግን አልቻለችም። ሄሮድስ በመጀመሪያ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ይጠብቀውም ነበር። ሄሮድስ የዮሐንስን ንግግር በሰማ ቊጥር ይታወክ ነበር፤ ይሁን እንጂ በደስታ ይሰማው ነበር። ሄሮድስ የተወለደበትን ቀን ለማክበር ለመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ ለጦር ሹማምንትና ለአንዳንድ የታወቁ የገሊላ ነዋሪዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ለሄሮዲያዳ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላት፤ ስለዚህም የሄሮዲያዳ ልጅ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገብታ እየጨፈረች ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ተጋባዦች አስደሰተች፤ ንጉሡም ልጅትዋን፦ “የምትፈልጊውን ማንኛውንም ነገር ጠይቂኝ፤ እሰጥሻለሁ” አላት፤ “የመንግሥቴንም እኩሌታ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ!” ሲል ማለላት። እርስዋም ወደ እናትዋ ሄዳ፥ “ምን ልጠይቅ?” አለቻት፤ እናትዋም “ ‘የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ይሰጠኝ፤’ ብለሽ ጠይቂ፤” አለቻት። ልጅትዋም ወዲያውኑ በፍጥነት ወደ ንጉሡ ተመልሳ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በሳሕን ሆኖ አሁን እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፤” ስትል ጠየቀች። ንጉሡ በዚህ ነገር በጣም አዘነ፤ ይሁን እንጂ በተጋባዦች ፊት ስላደረገው መሐላ የጠየቀችውን ሊከለክላት አልፈለገም። ስለዚህ ንጉሡ ወዲያውኑ አንዱን የዘብ ጠባቂ ወታደር የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ ላከው፤ ወታደሩም ወደ ወህኒው ቤት ሄዶ የዮሐንስን ራስ ቈረጠ፤ የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አድርጎ አመጣና ለልጅትዋ ሰጣት፤ ልጅትዋም ለእናትዋ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት።
ማርቆስ 6:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፥ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፥ “የዚህ ዓይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፥ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፥ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፥ እኔ ራሱን ያስቆረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷአል አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፥ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፥ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያዳምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምንቱ፥ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው፤ ንጉሡም ብላቴናዪቱን፥ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሓላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፥ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፥ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ አዘነ፤ በተጋበዙት እንግዶች ፊት የመሐላ ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ስለዚህ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፥ የዮሐንስን ራስ ቆርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቆረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት።