ማርቆስ 6:1-6
ማርቆስ 6:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና “እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን?” አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር።
ማርቆስ 6:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፣ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ! ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፣ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በቤተ ሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለ ማመናቸውም ተደነቀ።
ማርቆስ 6:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና፦ እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር።
ማርቆስ 6:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። በሰንበት ቀን በምኲራብ ማስተማር ጀመረ፤ ብዙ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ይሰሙት ነበር፤ እነርሱም “ይህ ሰው ይህን ሁሉ ነገር ከየት አገኘው? ምን ዐይነት ጥበብ ተሰጥቶታል? እነዚህንስ ተአምራት የሚያደርገው እንዴት ነው?” እያሉ ይደነቁ ነበር። ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፥ “ነቢይ በሌሎች ዘንድ ይከበራል፤ በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹና በቤተ ሰቡ መካከል ግን ይናቃል፤” ሲል መለሰላቸው። በዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር ሌላ ተአምር ማድረግ አልቻለም። ሕዝቡ ሳያምኑ በመቅረታቸው እጅግ ተገረመ፤ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር።
ማርቆስ 6:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፥ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፥ የያዕቆብና የዮሳ፥ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፥ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹ መካከል በቤተሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር።