ማርቆስ 4:21-34
ማርቆስ 4:21-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም አላቸው “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” አላቸውም “ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” እርሱም አለ፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም፤ ይነሣልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።” እርሱም አለ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፤ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች፤ ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።” መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፤ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።
ማርቆስ 4:21-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንዲህም አላቸው፤ “መብራት ተወስዶ ከእንቅብ በታች ወይም ከዐልጋ ሥር ይቀመጣልን? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለምን? ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።” በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው። ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።” ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋራ እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።” ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።
ማርቆስ 4:21-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም አላቸው፦ መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። አላቸውም፦ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል። እርሱም አለ፦ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች። መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።
ማርቆስ 4:21-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ሰው መብራትን አብርቶ በእንቅብ ውስጥ ወይም በአልጋ ሥር ያስቀምጠዋልን? የሚያስቀምጠው፥ ብርሃኑ በሚታይበት በመቅረዝ ላይ አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል፤ በይበልጥም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ዘር የሚዘራውን ሰው ትመስላለች። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀንም ይነቃል፤ እንዴት እንደ ሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋልም። ምድሪቱም በገዛ ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፥ ቀጥሎም ዛላውን ታሳያለች፤ በኋላም በዛላው ፍሬ ይገኛል። ሰብሉም በደረሰ ጊዜ መከር በመሆኑ ሰውየው ወዲያውኑ ማጭድ ያዘጋጃል።” ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንገልጻታለን? የሰናፍጭን ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ ስትዘራ በምድር ላይ ካለው ዘር ሁሉ ያነሰች ናት። ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከአትክልት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በሥርዋ ጎጆ ሠርተው መጠለል እስኪችሉ ድረስ ታላላቅ ቅርንጫፎችን ታወጣለች።” ኢየሱስም ሰዎች ማስተዋል በሚችሉበት መጠን፥ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ቃሉን ይነግራቸው ነበር። ያለ ምሳሌም አያስተምራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን ሲሆኑ ግን ሁሉን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ ያስረዳቸው ነበር።
ማርቆስ 4:21-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም አላቸው “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” አላቸውም “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” እርሱም እንዲህ አለ፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም፤ ይነሣልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷአልና ወዲያው ማጨድ ይጀምራል።” እርሱም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፤ እርሷም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች፤ ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታወጣለች።” መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፤ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀመዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።