የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 4:1-29

ማርቆስ 4:1-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ደግሞም በባሕር ዳር ሊያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በታንኳ ገብቶ በባሕር ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕር ዳር በምድር ላይ ነበሩ። በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፤ በትምህርቱም አላቸው። “ስሙ! እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፤ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው፤ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፤ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፤” አለ። ብቻውንም በሆነ ጊዜ በዙሪያው የነበሩት ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እንዲህም አላቸው “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ ‘አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፤ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፤ እንዳይመለሱ ኀጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው’ ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል።” አላቸውም “ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ለጊዜው ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፤ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፤ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።” እንዲህም አላቸው “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” አላቸውም “ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” እርሱም አለ፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም፤ ይነሣልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።”

ማርቆስ 4:1-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሌላ ጊዜ ደግሞ በባሕሩ አጠገብ ያስተምር ጀመር። እርሱ ባለበት አካባቢ እጅግ ብዙ ሕዝብ ስለ ተሰበሰበ፣ በባሕሩ ላይ ወዳለች ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ባለው ስፍራ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም ብዙ ነገሮችን በምሳሌ አስተማራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ አንዳንዱ ዘር መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። ሌላውም ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስድሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ብቻውን በሆነ ጊዜ፣ ዐሥራ ሁለቱና ዐብረውት የነበሩት ሌሎች ስለ ምሳሌዎቹ ጠየቁት። እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም፣ “ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣ መስማቱን እንዲሰሙ ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።” ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ነገር ግን ሥር ስላልሰደዱ፣ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።” እንዲህም አላቸው፤ “መብራት ተወስዶ ከእንቅብ በታች ወይም ከዐልጋ ሥር ይቀመጣልን? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለምን? ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።” በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው። ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።”

ማርቆስ 4:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ደግሞም በባሕር ዳር ሊያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በታንኳ ገብቶ በባሕር ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕር ዳር በምድር ላይ ነበሩ። በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፥ በትምህርቱም አላቸው፦ ስሙ። እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ። ብቻውንም በሆነ ጊዜ፥ በዙሪያው የነበሩት ከአሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እንዲህም አላቸው፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥ እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል። አላቸውም፦ ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፥ በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው። እንዲህም አላቸው፦ መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። አላቸውም፦ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።

ማርቆስ 4:1-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ እንደገና በባሕሩ አጠገብ ማስተማር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው እርሱ በባሕሩ ላይ በነበረው ጀልባ ገብቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ነበሩ። ብዙ ነገሮችንም በምሳሌ አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! እነሆ፥ ገበሬው ዘሩን ለመዝራት ወጣ፤ ሲዘራ ሳለ አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ ቦታውም ብዙ ዐፈር ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ የጠለቀ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም ባደገ ጊዜ ስላነቀው ያለ ፍሬ ቀረ። ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ ፍሬ ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም መቶ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ኢየሱስ ብቻውን በሆነ ጊዜ ይከተሉት የነበሩ ሰዎችና ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ስለ ምሳሌዎቹ ትርጒም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጪ ላሉት ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል። ይህም የሚሆነው፥ ‘እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ኃጢአታቸው ይቅር እንዳይባልላቸው፥ ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤ መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’ ” በተባለው መሠረት ነው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም ይህ ምሳሌ አይገባችሁምን? ታዲያ፥ ሌሎችን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ዘሪው ቃልን ይዘራል፤ ቃሉ በተዘራ ጊዜ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል የሚወስድባቸውን ሰዎች ነው። እንዲሁም በጭንጫማ ቦታ ላይ የተዘራው የሚያመለክተው ቃሉን ሲሰሙ ወዲያው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ግን እነርሱ ለጊዜው ነው እንጂ በልባቸው ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቃሉ ምክንያት ችግር ወይም ስደት ቢደርስባቸው ወዲያውኑ ተሰናክለው ይወድቃሉ። በእሾኽ መካከል የተዘራው ደግሞ የሚያመለክተው ቃሉን የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብ፥ የሀብት ፍቅርና ሌላውም ከንቱ ምኞት ወደ ልባቸው ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት የተዘራው ግን የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በማስተዋል የሚቀበሉትን ሰዎች ነው። እንዲህ ዐይነቱ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም መቶ ፍሬ ያፈራል። “ሰው መብራትን አብርቶ በእንቅብ ውስጥ ወይም በአልጋ ሥር ያስቀምጠዋልን? የሚያስቀምጠው፥ ብርሃኑ በሚታይበት በመቅረዝ ላይ አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል፤ በይበልጥም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ዘር የሚዘራውን ሰው ትመስላለች። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀንም ይነቃል፤ እንዴት እንደ ሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋልም። ምድሪቱም በገዛ ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፥ ቀጥሎም ዛላውን ታሳያለች፤ በኋላም በዛላው ፍሬ ይገኛል። ሰብሉም በደረሰ ጊዜ መከር በመሆኑ ሰውየው ወዲያውኑ ማጭድ ያዘጋጃል።”

ማርቆስ 4:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንደገናም በባሕር ዳርቻ ያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በባሕሩ ላይ በነበረች ጀልባ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ነበሩ። በምሳሌም ብዙ ነገር አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፤ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው፤ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ አደገ፤ አድጎም ፍሬ ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ስልሳ፥ አንዱም መቶ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ፤” አለ። ብቻውንም በሆነ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በዙሪያው የነበሩት ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም፥ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም፦ ተመልሰው ይቅር እንዳይላቸው፥ ‘ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤ መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’” አላቸው። እንዲህም ሲል ጠየቃቸው፦ “ይህን ምሳሌ ያልተረዳችሁ፥ እንዴት ሌሎችን ምሳሌዎች ሁሉ ታውቃላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃሉ በተዘራ ጊዜ በመንገድ ዳር የነበሩት፦ እነርሱ በሰሙት ጊዜ ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል የሚወስድባቸው ናቸው። እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ለጊዜው ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፤ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፤ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።” እንዲህም አላቸው “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” አላቸውም “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” እርሱም እንዲህ አለ፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ ሌሊትና ቀን ይተኛልም፤ ይነሣልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷአልና ወዲያው ማጨድ ይጀምራል።”