ማርቆስ 3:13-19
ማርቆስ 3:13-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለት አደረገ፤ ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፤ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን።
ማርቆስ 3:13-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለስብከትም ይልካቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤ አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣ ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ተቀናቃኙ ስምዖን፣ እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
ማርቆስ 3:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን።
ማርቆስ 3:13-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ እነዚያን የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡ። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፥ ለማስተማርም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡትም ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው ስምዖን፥ ቦአኔርጌስ ወይም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሠየማቸው፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ተቀናቃኙ ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውም አስቆሮታዊው ይሁዳ።
ማርቆስ 3:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲሆኑና ለመስበክም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” አላቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡት ዐሥራ ሁለቱም፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፤ ቦአኔርጌስ፥ ማለትም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሰየማቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስን፤ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርተሎሜውስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ቀነናዊው ስምዖን፥ እና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው።