የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 15:1-39

ማርቆስ 15:1-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “አንተ አልህ፤” ብሎ መለሰለት። የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። ጲላጦስም ደግሞ “አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። በዐመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። ጲላጦስም “የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን?” ብሎ መለሰላቸው፤ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ “እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ዳግመኛ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው?” አላቸው። እነርሱ ግን “ስቀለው!” እያሉ ጩኸት አበዙ። ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፤ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾህ አክሊልም ጐንጕነው ደፉበት፤ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን፤” እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ራሱንም በመቃ መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ ልብሱንም አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ሰቀሉትም፤ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሕፈትም “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ተጽፎ ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍም “ከዐመፀኞች ጋር ተቆጠረ፤” ያለው ተፈጸመ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና “ዋ! ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን፡” አሉ። እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤” አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው “እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ “ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ፤” እያለ አጠጣው። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱንም ሰጠ። የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፤” አለ።

ማርቆስ 15:1-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጧት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሓፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋር ወዲያው ከተማከሩ በኋላ፣ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፣ “አንተው አልኸው፣” በማለት መለሰለት። የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። ጲላጦስም፣ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ፤ በብዙ ነገር ከስሰውሃል” ሲል እንደ ገና ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ። በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ጲላጦስም፣ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። ጲላጦስም እንደ ገና፣ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም እንደ ገና፣ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ” አላቸው። እነርሱ ግን፣ “ስቀለው!” እያሉ የባሰ ጮኹ። ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት። ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤ ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጕሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ። ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሑፍም፣ “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ። በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዬ! ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ አንተ ነህ፤ እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን።” እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም፤ አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስቲ ከመስቀል ይውረድ።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ።

ማርቆስ 15:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፦ አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ አንተ አልህ ብሎ መለሰለት። የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። ጲላጦስም ደግሞ፦ አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። ጲላጦስም፦ የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ፦ እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። እነርሱም ዳግመኛ፦ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን፦ ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሕፈትም፦ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍም፦ ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፦ ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ፦ ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው፦ እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ፦ ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ፦ ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ።

ማርቆስ 15:1-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሸንጎውም አባሎች ሁሉ ጋር ተማከሩ፤ ከዚያም በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው፤” አለው። የካህናት አለቆች ግን ኢየሱስን በብዙ ይወነጅሉት ነበር። ስለዚህ ጲላጦስ “በስንት ነገር እንደሚከሱህ ተመልከት! ከቶ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ አሁንም ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠም። ጲላጦስ በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሰዎቹ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ይለቅላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ በመንግሥት ላይ ተነሣሥተው፥ ሰው በመግደል ወህኒ ቤት የገቡ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከነዚህም ዐመፀኞች አንዱ በርባን የሚባለው ሰው ነበር። ሕዝቡም ወደ ጲላጦስ ቀርበው የተለመደውን ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠየቁት። እርሱም “የአይሁድን ንጉሥ ፈትቼ እንድለቅላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። ይህንንም ያለው የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ስለ ነበር ነው። የካህናት አለቆች ግን፥ “በእርሱ ፈንታ በርባን ይፈታልን፤” ብለው ጲላጦስን እንዲጠይቁ ሰዎቹን አነሣሡ። ጲላጦስም፦ “ታዲያ፥ ይህን የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላድርገው?” ሲል ሰዎቹን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ እንደገና ጮኹ። ጲላጦስም “ለምን? ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ጲላጦስ ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን አስገረፈውና እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ የቀሩትንም ወታደሮች ሁሉ ጠሩ፤ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበትና፤ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ በማፌዝ እጅ ይነሡት ነበር። በመቃ ራስ ራሱን ይመቱት ነበር፤ ምራቃቸውንም እንትፍ ይሉበት ነበር፤ በፊቱም በማላገጥ እየተንበረከኩ ይሰግዱለት ነበር። ካፌዙበትም በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው፥ የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲሄዱም ሳሉ የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ትርጒሙ የራስ ቅል ወደ ሆነው ስፍራ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። እዚያም ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም። ከዚህም በኋላ ሰቀሉት፤ ልብሶቹንም ማን ምን እንደሚወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት። ኢየሱስን ሲሰቅሉት ጊዜው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። ወንጀሉንም ለማመልከት “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር። ከኢየሱስም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አምጥተው አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። [ በዚህም ሁኔታ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤” የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጸመ።] በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች ራሳቸውን በንቀት እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር፦ “አዬ፥ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” በዚህ ዐይነት የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራንም እርስ በርሳቸው እንዲህ እየተባባሉ ይዘባበቱበት ነበር፦ “ሌሎችን አድኖአል፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንይና እንመንበት!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር። ከቀኑም ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ የእርሱን ጩኸት ሰምተው “እነሆ! ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። ከእነርሱም አንዱ ሮጠና ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ፤ እንዲጠጣውም በመቃ ላይ አድርጎ ለኢየሱስ ሰጠውና “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደ ሆነ እንይ!” አለ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱም ከሥጋው ተለየች። የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። በመስቀሉ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረ የመቶ አለቃ ኢየሱስ እንዴት ነፍሱ ከሥጋው እንደ ተለየች ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፤” አለ።

ማርቆስ 15:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፥ ከጸሓፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋር ወዲያው ከተማከሩ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፥ “አንተው አልኸው፥” በማለት መለሰለት። የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። ጲላጦስም፥ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ በብዙ ነገር ከሰውሃል” ሲል እንደገና ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ። በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ጲላጦስም፥ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። ጲላጦስም እንደገና፥ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም እንደገና፥ “ስቀለው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፥ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ?” አላቸው። እነርሱ ግን፥ “ስቀለው” እያሉ የባሰ ጮኹ። ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾክ አክሊል ጐንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት። ከዚያም፥ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ እጅ ነሡት፤ ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም ኢየሱስን፥ ትርጉሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሑፍም፥ “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍ፥ “ከዐመፀኞች ጋር ተቆጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ። በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አይ፥ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ አንተ ነህ፤ እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን።” እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም፤ አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፥ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስቲ ከመስቀል ይውረድ።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፥ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፥ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ከዚያም፥ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ።