ማርቆስ 14:44-72

ማርቆስ 14:44-72 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት፤” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና “መምህር ሆይ! መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው፤ እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ፤ ጆሮውንም ቈረጠ። ኢየሱስም መልሶ “ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ፤” አላቸው። ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፤ ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ። ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፤ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፤ ምስክርነታቸው ግን አልተስማማም። ሰዎችም ተነሥተው “እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ፤ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ፤” ሲል ሰማነው፤ ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተስማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ “አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው?” ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ፤ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና “የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና “ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ። እነርሱም ሁሉ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና “ትንቢት ተናገር፤” ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና “አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ፤” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም፤ አላስተውልምም፤” ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው፤” ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን “የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም፤” ብሎ እራሱን ይረግምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስንም ኢየሱስ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:44-72 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አሳልፎ የሚሰጠውም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። እንደ ደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው፤ ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቈመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋራ ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተዉት ሸሹ። ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፣ ግልድሙን ጥሎ ዕራቍቱን ሸሸ። ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፣ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከጠባቂዎቹ ጋራ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ “የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፣ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ጠባቂዎቹም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፣ ከሊቀ ካህናቱ የቤት ሠራተኞች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋራ ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን፣ “የምትዪውን እኔ ዐላውቀውም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ አለ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ሠራተኛዪቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፣ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደ ገና ተናገረች። እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፣ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፣ በርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፣ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:44-72 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አሳልፎ የሚሰጠውም፦ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና፦ መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። ኢየሱስም መልሶ፦ ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ። ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። ሰዎችም ተነሥተው፦ እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ፦ አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና፦ የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፦ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ስድቡን ሰማችሁ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ፦ ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና፦ ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና፦ አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት፦ ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን፦ የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። እርሱ ግን፦ ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስንም ኢየሱስ፦ ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:44-72 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አሳልፎ የሚሰጠውም ይሁዳ፥ “እናንተ የምትይዙት እኔ ሰላምታ ሰጥቼ የምስመውን ነው፤ እርሱን በጥንቃቄ ይዛችሁ ውሰዱት፤” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው። ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ያዙት። እዚያ ቆመው ከነበሩት ከኢየሱስ ተከታዮች አንዱ ሰይፉን መዝዞ የካህናት አለቃውን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን እንደ ወንበዴ ለመያዝ ነውን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ የሆነው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዲፈጸም ነው።” ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ትተውት ሸሹ። የበፍታ ነጠላ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት ግን ኢየሱስን ይከተል ነበር፤ ሰዎቹም በያዙት ጊዜ ነጠላውን ጥሎ ራቁቱን ሸሽቶ አመለጠ። ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም። የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። ኢየሱስም “አዎ፥ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታያላችሁ! እንዲሁም በሰማይ ደመና ተመልሶ ሲመጣ ታያላችሁ” አለ። የካህናት አለቃውም በቊጣ ልብሱን ቀደደና “ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? እነሆ! ይህን የስድብ ቃል በእግዚአብሔር ላይ ሲሰነዝር ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” አለ። ሁሉም በአንድ ቃል፥ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ምራቃቸውን እንትፍ ይሉበት ጀመር፤ ዐይኑንም በጨርቅ ሸፍነው “አንተ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደ መታህ ዕወቅ!” እያሉ በቡጢ ይመቱት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ ከካህናት አለቃው ቤት በታች በግቢው ውስጥ እንዳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንድዋ መጣች፤ እርስዋ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኲር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ፤” አለችው። እርሱ ግን “እኔ አላውቅም፤ አንቺ የምትዪውም አይገባኝም፤” ሲል ካደ። ይህንንም ብሎ ወደ ደጃፉ እንደ ወጣ ዶሮ ጮኸ። ገረዲትዋም ጴጥሮስን አይታ፥ በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው!” ስትል እንደገና ትናገር ጀመር፤ እርሱ ግን እንደገና ካደ። ጥቂት ቈየት ብሎም በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው መሆንህን በእርግጥ አነጋገርህ ያስረዳል፤ ስለዚህ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። ወዲያውኑ ዶሮ ሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለውና ምርር ብሎ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:44-72 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አሳልፎ የሚሰጠውም፥ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷአቸው ነበር። እንደደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ “መምህር ሆይ” ብሎ ሳመው፤ ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም። በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቆረጠ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቆመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ጣል ያደረገ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፥ በፍታውን ጥሎ ዕራቁቱን ሸሸ። ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፥ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፥ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፥ የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፥ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፥ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፥ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና፥ የቡሩኩ ልጅ፥ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፥ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፥ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?”፤ እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፥ “እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፥ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና፥ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። እርሱ ግን፥ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፥ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ተናገረች። እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፥ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፥ በእርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱ ግን፥ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፥ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።