ማርቆስ 14:12-21

ማርቆስ 14:12-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የፋሲካን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ?” አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “ወደ ከተማ ሂዱ፤ ማድጋ ውኀ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ተከተሉት። የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል፤’ በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤በዚያም አሰናዱልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጡ፤ ወደከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል፤” አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አላቸው።

ማርቆስ 14:12-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ የውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነት ላይ ተነጥፎ የተሰናዳ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ ዐብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።”

ማርቆስ 14:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም፦ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው።

ማርቆስ 14:12-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የፋሲካውን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “የፋሲካን ራት ለመብላት ወዴት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እዚያም የውሃ እንሥራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከተሉት፤ ወደሚገባበትም ቤት ሂዱና የቤቱን ጌታ፥ ‘መምህር፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት ለእኔ የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው?’ ይላል በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን የተዘጋጀውንና የተነጠፈውን ትልቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከዚያ ወጥተው ወደ ከተማው ሄዱ፤ ልክ ኢየሱስ እንዳላቸውም አገኙ፤ የፋሲካንም ራት በዚያ አዘጋጁ። በመሸ ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ፤ በገበታ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤ እርሱም አሁን ከእኔ ጋር ራት በመብላት ላይ የሚገኘው ነው፤” አለ። እነርሱም በዚህ ነገር አዝነው “እኔ እሆንን?” እያሉ ተራ በተራ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ያ ሰው ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ የሆነው አሁን ከእኔ ጋር በዚህ ሳሕን ውስጥ ወጥ የሚያጠቅሰው ነው፤ የሰው ልጅ አስቀድሞ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰውስ ቀድሞውኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር!”

ማርቆስ 14:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፥ ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፥ መምህሩ፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?” ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ፥ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም አዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፥ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት፤ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”