የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 14:1-52

ማርቆስ 14:1-52 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም፣ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሠራ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፣ ብልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አፈሰሰችው። በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን እንደዚህ በከንቱ ይባክናል? ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፣ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፣ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ አልኖርም፤ እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ የውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነት ላይ ተነጥፎ የተሰናዳ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ ዐብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ከወይን ፍሬ አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ’ ከተነሣሁ በኋላ ግን፣ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለ። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋራ ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ከርሱ ጋራ ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ ቢቻል ሰዓቱ ከርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፣ “አባ፣ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፣ “ስምዖን ሆይ፤ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየ። ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደ ተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል! ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል! ተነሡ፤ እንሂድ! እነሆ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።” ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ዐብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፣ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። እንደ ደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው፤ ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቈመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋራ ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተዉት ሸሹ። ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፣ ግልድሙን ጥሎ ዕራቍቱን ሸሸ።

ማርቆስ 14:1-52 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። “የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን፤” ይሉ ነበርና። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶችም “ይህ የሽቶ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና፤” ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ “ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።” ከዐሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው፤ ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። የፋሲካን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ?” አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “ወደ ከተማ ሂዱ፤ ማድጋ ውኀ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ተከተሉት። የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል፤’ በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤በዚያም አሰናዱልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጡ፤ ወደከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል፤” አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና “እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም፤” አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። ኢየሱስም “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛዉን እመታለሁ፤ በጎችም ይበተናሉ፤’ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ “ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም፤” አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ፤ ትጉም፤” አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና “አባ አባት ሆይ! ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን፤” አለ። መጣም፤ ተኝተውም አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም “ስምዖን ሆይ! ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አለው። ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። ደግሞም መጥቶ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አላወቁም። ሦስተኛም መጥቶ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል፤” አላቸው። ወዲያውም ገና ሲናገር ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት፤” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና “መምህር ሆይ! መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው፤ እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ፤ ጆሮውንም ቈረጠ። ኢየሱስም መልሶ “ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ፤” አላቸው። ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፤ ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።

ማርቆስ 14:1-52 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶችም፦ ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም፦ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። ኢየሱስም፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም፦ ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ፦ ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና፦ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና፦ አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም፦ ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው፥ ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። ሦስተኛም መጥቶ፦ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም፦ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና፦ መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። ኢየሱስም መልሶ፦ ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።

ማርቆስ 14:1-52 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የአይሁድ የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስን በተንኰል ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ ሁከት ያነሣሣል በማለት “በበዓል ቀን ይህን አናደርግም፤” አሉ። ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበር። በገበታም ቀርቦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነና የከበረ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት፥ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡን ሰብራ ሽቶውን በኢየሱስ ራስ ላይ አፈሰሰችው። እዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው፦ “ይህ ሽቶ በከንቱ መባከኑ ለምንድን ነው? ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ሊሰጥ ይቻል ነበር!” ተባባሉ፤ ሴቲቱንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት! ስለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለ ሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አታገኙኝም፤ ይህች ሴት የተቻላትን አድርጋለች፤ ሥጋዬም ከመቀበሩ በፊት አስቀድማ ለማዘጋጀት ሽቶ ቀባችው። በእውነት እላችኋለሁ፤ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያ ይነገርላታል።” ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ አስቆሮታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ባወቁ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ቃል ገቡለት። እርሱም ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካውን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “የፋሲካን ራት ለመብላት ወዴት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እዚያም የውሃ እንሥራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከተሉት፤ ወደሚገባበትም ቤት ሂዱና የቤቱን ጌታ፥ ‘መምህር፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት ለእኔ የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው?’ ይላል በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን የተዘጋጀውንና የተነጠፈውን ትልቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከዚያ ወጥተው ወደ ከተማው ሄዱ፤ ልክ ኢየሱስ እንዳላቸውም አገኙ፤ የፋሲካንም ራት በዚያ አዘጋጁ። በመሸ ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ፤ በገበታ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤ እርሱም አሁን ከእኔ ጋር ራት በመብላት ላይ የሚገኘው ነው፤” አለ። እነርሱም በዚህ ነገር አዝነው “እኔ እሆንን?” እያሉ ተራ በተራ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ያ ሰው ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ የሆነው አሁን ከእኔ ጋር በዚህ ሳሕን ውስጥ ወጥ የሚያጠቅሰው ነው፤ የሰው ልጅ አስቀድሞ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰውስ ቀድሞውኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር!” እነርሱ በመብላት ላይ ሳሉ ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፥ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከጽዋው ጠጡ። እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የቃል ኪዳን ደሜ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከአዲሱ ወይን እስክጠጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም።” ከዚያም በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ ‘እረኛውን መትቼ እገድላለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ፤’ ተብሎ ተጽፎአልና ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ፤ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ትታችሁኝም ትሸሻላችሁ፤ ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ፥ እኔ ከቶ አልክድህም!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “መሞት እንኳ ቢያስፈልግ ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” እያለ አጠንክሮ ተናገረ። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት እንዲሁ ይሉ ነበር። ከዚህም በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም አስከትሎ ሄደ፤ እዚያም እጅግ ያዝንና ይጨነቅ ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዝናለች፤ እዚህ ቈዩ፤ ተግታችሁም ጠብቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ፤ በመሬትም ላይ በግንባሩ ተደፍቶ የሚቻል ቢሆን ያቺ ሰዓት እንድታልፍለት ጸለየ። እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፥ ሁሉ ነገር ይቻልሃል፤ ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን።” ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ ጴጥሮስን፦ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት እንኳ ልትነቃ አልቻልክምን?” አለው። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አላቸው። እንደገናም ሄዶ፥ ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ጸለየ። ደግሞም ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር፥ ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛም ጊዜ ወደ እነርሱ መጥቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን? እንግዲህስ በቃ! ሰዓቱ ደርሶአል! እነሆ! የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። በሉ ተነሡ! እንሂድ! አሳልፎ የሚሰጠኝ ይኸው ቀርቦአል!” ወዲያውም ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ የተላኩ ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም ይሁዳ፥ “እናንተ የምትይዙት እኔ ሰላምታ ሰጥቼ የምስመውን ነው፤ እርሱን በጥንቃቄ ይዛችሁ ውሰዱት፤” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው። ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ያዙት። እዚያ ቆመው ከነበሩት ከኢየሱስ ተከታዮች አንዱ ሰይፉን መዝዞ የካህናት አለቃውን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን እንደ ወንበዴ ለመያዝ ነውን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ የሆነው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዲፈጸም ነው።” ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ትተውት ሸሹ። የበፍታ ነጠላ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት ግን ኢየሱስን ይከተል ነበር፤ ሰዎቹም በያዙት ጊዜ ነጠላውን ጥሎ ራቁቱን ሸሽቶ አመለጠ።

ማርቆስ 14:1-52 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፥ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም፥ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፥ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አርከፈከፈችው። በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቆጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፥ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፥ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። ድኾች ምንም ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፥ ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፥ መምህሩ፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?” ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ፥ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም አዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፥ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት፤ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፥ “እንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው፤ ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ” ከተነሣሁ በኋላ ግን፥ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ። ጴጥሮስም፥ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ። ኢየሱስም፥ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፥ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቆዩ” አላቸው። ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ፥ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፥ “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየው። ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቷል።” ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ አብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፥ ከካህናት አለቆች፥ ጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም፥ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷአቸው ነበር። እንደደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ “መምህር ሆይ” ብሎ ሳመው፤ ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም። በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቆረጠ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቆመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ። ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ጣል ያደረገ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፥ በፍታውን ጥሎ ዕራቁቱን ሸሸ።