ማርቆስ 1:14-28

ማርቆስ 1:14-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና “ዘመኑ ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሐ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ፤” እያለ ወደ ገሊላ መጣ። በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። ኢየሱስም “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ፤” አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። ወዲያውም ጠራቸው፤ አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ እርሱም “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ! የእግዚአብሔር ቅዱሱ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም “ዝም በል፤ ከእርሱም ውጣ፤” ብሎ ገሠጸው። ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። ሁሉም “ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው?” ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።

ማርቆስ 1:14-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄዶ፣ “ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ!” እያለ ይሰብክ ነበር። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፣ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ትንሽ ዕልፍ እንዳለ፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፣ ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም አባታቸውን በጀልባው ላይ ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋራ ትተው ተከተሉት። ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሐፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። በዚያ ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ከርሱ ወጣ። ሁሉም በመገረም፣ “ይህ ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ወጣ።

ማርቆስ 1:14-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ። በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። ኢየሱስም፦ በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። ወዲያውም ጠራቸው አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። ሁሉም፦ ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።

ማርቆስ 1:14-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዮሐንስም ተይዞ ወደ እስር ቤት ከገባ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። ሲያስተምርም፦ “ዘመኑ ተፈጽሞአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ! በወንጌልም እመኑ!” ይል ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፦ “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችንም እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ፤” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም ጥቂት አለፍ እንዳለ፥ ሌሎች ሁለት ወንድማማችን አየ፤ እነርሱም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ፤ እነርሱ በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ይጠግኑ ነበር፤ ኢየሱስ ወዲያውኑ ጠራቸው፤ እነርሱም አባታቸውን ዘብዴዎስን ከሠራተኞቹ ጋር በጀልባው ላይ ትተውት ኢየሱስን ተከተሉት። አልፈውም ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ደረሱ፤ ወዲያው በሚቀጥለውም ሰንበት ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። ኢየሱስ፥ የሕግ መምህራን እንደሚያስተምሩት ዐይነት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ የሰሙት ሁሉ በትምህርቱ ተደነቁ። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበት በምኲራባቸው የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።” ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ “ጸጥ ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ እየጮኸ ከእርሱ ወጣ። “ይህ ምንድን ነው? ምን ዐይነት አዲስ ትምህርት ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ በሥልጣኑ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤” እያሉ ሁሉም በመገረም እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ወዲያውኑ፥ የኢየሱስ ዝና በገሊላ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ ተሰማ።

ማርቆስ 1:14-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። “ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” እያለ ይሰብክ ነበር። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፥ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፥ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ትንሽ እልፍ እንዳለ፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፥ ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር አባታቸውን በጀልባው ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሓፍት ሳይሆን፥ እንደ ባለ ሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! ከኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፥ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኃይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ። ሕዝቡ በሙሉ በመደነቅ፥ “ይህ ምንድነው? በሥልጣን ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤ ይህ አዲስ ትምህርት ምንድነው?” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ።