የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 4:1-11

ማቴዎስ 4:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ፦ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፦ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።

ማቴዎስ 4:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ፥ ኢየሱስ በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ በረሓ ወሰደው። እዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። ፈታኙ ወደ ኢየሱስ መጥቶ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። ኢየሱስ ግን “ ‘ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ፥ በእንጀራ ብቻ አይደለም’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው። ከዚህ በኋላ፥ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቤተ መቅደስ ጣራ ጫፍ ላይ አቆመው፤ “ ‘እግሮችህ በድንጋይ እንዳይሰናከሉ፥ በእጆቻቸው ይደግፉህ ዘንድ መላእክቱን ያዝልሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደታች ራስህን ወርውር” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። እንደገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን በጣም ከፍ ወዳለ ተራራ ላይ አውጥቶ፥ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ከነክብራቸው አሳየውና፤ “ተደፍተህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። የዚያን ጊዜ ኢየሱስ “ ‘ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ!’ ተብሎ ተጽፎአልና ወግድ አንተ ሰይጣን!” አለው። ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ተወው፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።

ማቴዎስ 4:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል!” አለው። እርሱም መልሶ “ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ “ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር” አለው። ኢየሱስም “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ “ሂድ፤ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው። ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።

ማቴዎስ 4:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። ፈታኙም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት። ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣ በእጃቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል።’ ” ኢየሱስም፣ “እንደዚሁም በመጻሕፍት፣ ‘እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ተጽፏል” በማለት መለሰለት። እንደ ገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ አወጣው፤ የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።

ማቴዎስ 4:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በዲያብሎስ እንዲፈተን መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። ፈታኙ መጥቶ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። እርሱ ግን “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ በመቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመውና “‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ራስህን ወደ ታች ወርውር” አለው። ኢየሱስም “‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። እንደገና ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየውና፥ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “ሂድ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆ መላእክት መጥተው አገለገሉት።