ማቴዎስ 24:3-14
ማቴዎስ 24:3-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዐመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
ማቴዎስ 24:3-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ በማለት በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሆኖም መጨረሻው ገና ስለሆነ በዚህ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኋል፤ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም። ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ። ክፋት ስለሚገንን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።
ማቴዎስ 24:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
ማቴዎስ 24:3-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? የመምጫህና የዘመኑ መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም ሰው እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ። የጦርነትን ድምፅና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ ይህ ሁሉ መሆን ስላለበት አትደንግጡ፤ መጨረሻው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል። ይህም ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋል፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በመላው ዓለም ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል።
ማቴዎስ 24:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘መሢሑ እኔ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ አስተውሉ፥ አትደንግጡ፥ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብና የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከሕገ ወጥነት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል።