ማቴዎስ 24:26-44

ማቴዎስ 24:26-44 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እንግዲህ ‘እነሆ፥ በበረሀ ነው፤’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በእልፍኝ ነው፤’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቍኦጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውሃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውሃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። “ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፤ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።

ማቴዎስ 24:26-44 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ፤ በረሓው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል። በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናጋሉ።’ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤ እርሱም መላእክቱን ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋራ ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱ ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ። “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም። “ነገር ግን ስለዚያች ቀንና ሰዓት ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። በዚያ ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች። “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤቱ ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። ስለዚህ የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል፤ እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።

ማቴዎስ 24:26-44 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቍኦጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቍኦፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።

ማቴዎስ 24:26-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስለዚህ ‘እነሆ፥ በበረሓ አለ!’ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በስውር ቦታ አለ!’ ቢሉአችሁ አትመኑ። መብረቅ በሰማይ ብልጭ ብሎ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። በድን ወደአለበት ቦታ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ያለቅሳሉ። የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ያዩታል፤ ታላቅ የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰሙ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም የዓለም ማዕዘኖች ሄደው ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ያሉትን የእርሱን ምርጥ ሰዎች ይሰበስባሉ።” “የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ፥ ያ ጊዜ በጋ መቅረቡን ታውቃላችሁ። እንዲሁም እናንተ ይህን ሁሉ ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዕወቁ። በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።” “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው ዐይነት፥ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ዘመን፥ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያጋቡና ሲያጋቡ ነበር። የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከ ወሰዳቸው ድረስ አላወቁም ነበር፤ የሰው ልጅ አመጣጥም ልክ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ አብረው ይሠራሉ። አንደኛው ይወሰዳል ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንደኛዋ ትወሰዳለች፤ ሌላይቱ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ። ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። እንዲሁም የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።”

ማቴዎስ 24:26-44 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ ‘እነሆ በበረሀ አለ’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ በቤት ውስጥ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ቀናት መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይሎችም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ነገዶች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ጋር ይልካቸዋል፤ የእርሱን ምርጦች ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ይሰበስባሉ። “ምሳሌውን ከበለስ ዛፍ ተማሩ፤ ቅርጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠሎችዋም ሲያቆጠቁጡ፥ ያንጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና። ከጥፋት ውሃ በፊት በነበሩት ከእነዚያ ቀናት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩና፥ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ እንዳላወቁት፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች አንዷ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ። “ነገር ግን ይህን እወቁ፤ ባለቤት ሌባ ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።