የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 24:23-31

ማቴዎስ 24:23-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ፥ ክርስቶስ እዚህ አለ፤’ ወይም ‘እዚያ አለ፤’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ ‘እነሆ፥ በበረሀ ነው፤’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በእልፍኝ ነው፤’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።

ማቴዎስ 24:23-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ። እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። “ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ በረሓው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል። በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኅይላትም ይናጋሉ።’ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱም ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ።

ማቴዎስ 24:23-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።

ማቴዎስ 24:23-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“በዚያን ጊዜ ማንም ሰው ‘እነሆ፥ መሲሕ እዚህ አለ!’ ወይም ‘እዚያ አለ!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የእግዚአብሔርን ምርጦች እንኳ ለማሳሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። “እንግዲህ ይህን ሁሉ ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ ስለዚህ ‘እነሆ፥ በበረሓ አለ!’ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በስውር ቦታ አለ!’ ቢሉአችሁ አትመኑ። መብረቅ በሰማይ ብልጭ ብሎ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። በድን ወደአለበት ቦታ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ያለቅሳሉ። የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ያዩታል፤ ታላቅ የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰሙ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም የዓለም ማዕዘኖች ሄደው ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ያሉትን የእርሱን ምርጥ ሰዎች ይሰበስባሉ።”

ማቴዎስ 24:23-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ መሢሑ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳት ታላላቅ ምልክትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። ስለዚህ ‘እነሆ በበረሀ አለ’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ በቤት ውስጥ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ቀናት መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይሎችም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ነገዶች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ጋር ይልካቸዋል፤ የእርሱን ምርጦች ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ይሰበስባሉ።