ማቴዎስ 24:1-51
ማቴዎስ 24:1-51 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፤” አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዐመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ፥ ክርስቶስ እዚህ አለ፤’ ወይም ‘እዚያ አለ፤’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ ‘እነሆ፥ በበረሀ ነው፤’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በእልፍኝ ነው፤’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቍኦጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውሃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውሃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። “ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፤ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ ባሪያ ግን ‘ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል፤’ ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር፥ ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፤ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ማቴዎስ 24:1-51 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ፣ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱ ግን፣ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲሁ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም” አላቸው። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ በማለት በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሆኖም መጨረሻው ገና ስለሆነ በዚህ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኋል፤ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም። ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ። ክፋት ስለሚገንን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል። “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተነገረው፣ ‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል። በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚገኙ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ የሚገኝ ማንም ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ፤ በዕርሻ ቦታው የሚገኝ ማንም ሰው ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! እንግዲህ ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል። ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበረ፤ ስለተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ። እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። “ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ በረሓው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል። በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኅይላትም ይናጋሉ።’ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱም ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ። “ከበለስ ዛፍ ይህን ትምህርት ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም። “ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች። “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ። “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ እንግዲህ ማነው? ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ አገልጋይ ክፉ ቢሆንና ለራሱ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣ ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ እርሱ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ማቴዎስ 24:1-51 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቍኦጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቍኦፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ ባሪያ ግን፦ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ማቴዎስ 24:1-51 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱ ግን “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? በእውነት እላችኋለሁ፤ አንዳችም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ ሳይፈርስ የሚቀር የለም” አላቸው። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? የመምጫህና የዘመኑ መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም ሰው እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ። የጦርነትን ድምፅና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ ይህ ሁሉ መሆን ስላለበት አትደንግጡ፤ መጨረሻው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል። ይህም ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋል፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በመላው ዓለም ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል። “ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ባያችሁ ጊዜ አንባቢው ያስተውል! በዚያን ጊዜ በይሁዳ አገር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። በጣራ ላይ ያለ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ አይውረድ። በእርሻም ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ፤ በዚያን ጊዜ ለነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ! በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ፥ ወደፊትም እርሱን የሚመስል ከቶ የማይሆን፥ ታላቅ መከራ ይሆናል። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩማ ኖሮ አንድም ሰው መዳን ባልቻለ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። “በዚያን ጊዜ ማንም ሰው ‘እነሆ፥ መሲሕ እዚህ አለ!’ ወይም ‘እዚያ አለ!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የእግዚአብሔርን ምርጦች እንኳ ለማሳሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። “እንግዲህ ይህን ሁሉ ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ ስለዚህ ‘እነሆ፥ በበረሓ አለ!’ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በስውር ቦታ አለ!’ ቢሉአችሁ አትመኑ። መብረቅ በሰማይ ብልጭ ብሎ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። በድን ወደአለበት ቦታ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ያለቅሳሉ። የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ያዩታል፤ ታላቅ የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰሙ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም የዓለም ማዕዘኖች ሄደው ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ያሉትን የእርሱን ምርጥ ሰዎች ይሰበስባሉ።” “የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ፥ ያ ጊዜ በጋ መቅረቡን ታውቃላችሁ። እንዲሁም እናንተ ይህን ሁሉ ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዕወቁ። በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።” “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው ዐይነት፥ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ዘመን፥ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያጋቡና ሲያጋቡ ነበር። የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከ ወሰዳቸው ድረስ አላወቁም ነበር፤ የሰው ልጅ አመጣጥም ልክ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ አብረው ይሠራሉ። አንደኛው ይወሰዳል ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንደኛዋ ትወሰዳለች፤ ሌላይቱ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ። ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። እንዲሁም የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።” “ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጣቸው፥ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ ማን ነው? ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ያን አገልጋይ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ አገልጋይ ግን፥ ‘ጌታዬ አሁን አይመጣም ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና የሥራ ጓደኞቹን መደብደብ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፤ ያንን አገልጋይ ጌታው ይቀጣዋል፤ ዕጣ ክፍሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
ማቴዎስ 24:1-51 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀመዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የሚቀር የለም።” በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘መሢሑ እኔ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ አስተውሉ፥ አትደንግጡ፥ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ ራብና የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያ ናቸው። “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከሕገ ወጥነት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል። “ስለዚህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በጣራ ላይ ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ሊወስድ ወደ ኋላው አይመለስ። በነዚያ ቀናት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ መሢሑ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳት ታላላቅ ምልክትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። ስለዚህ ‘እነሆ በበረሀ አለ’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ በቤት ውስጥ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ቀናት መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይሎችም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ነገዶች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ጋር ይልካቸዋል፤ የእርሱን ምርጦች ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ይሰበስባሉ። “ምሳሌውን ከበለስ ዛፍ ተማሩ፤ ቅርጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠሎችዋም ሲያቆጠቁጡ፥ ያንጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና። ከጥፋት ውሃ በፊት በነበሩት ከእነዚያ ቀናት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩና፥ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ እንዳላወቁት፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች አንዷ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ። “ነገር ግን ይህን እወቁ፤ ባለቤት ሌባ ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። “ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጣቸው፥ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልህ ባርያ ማን ነው? ጌታው ሲመጣ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ የተባረከ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ነገር ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ ክፉ ባርያ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባርያዎች መደብደብ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባርያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፤ ለሁለት ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።