ማቴዎስ 23:23-39
ማቴዎስ 23:23-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዐመፀኝነት ሞልቶባችኋል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር፤’ ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች! የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችኋል። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል። “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና፥ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።”
ማቴዎስ 23:23-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ እናንተ የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጸዳላችሁ፤ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ሥሥት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፤ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ውጫቸው በኖራ ተለስነው የሚያምሩ፣ ውስጣቸው ግን በሙታን ዐፅምና በብዙ ርኩሰት የተሞላ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ! እናንተም በውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በክፋት የተሞላ ነው። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር እየገነባችሁ፣ የጻድቃንንም ሐውልት እያስጌጣችሁ፣ ‘በአባቶቻችን ዘመን ብንኖር ኖሮ፣ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁና። በዚህም የነቢያት ገዳዮች ለነበሩት አባቶቻችሁ ልጆች መሆናችሁን በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እንግዲህ የአባቶቻችሁን ጅምር ተግባር ከፍጻሜ አድርሱ! “እናንተ እባቦች፤ የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ልታመልጡ ትችላላችሁ? ስለዚህ ነቢያትን፣ ጠቢባንንና መምህራንን እልክላችኋለሁ፤ ከነዚህም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ ሌሎቹንም በምኵራቦቻችሁ ትገርፏቸዋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ታሳድዷቸዋላችሁ። ስለዚህ፣ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፣ በምድር ላይ ለፈሰሰው ንጹሕ ደም ሁሉ እናንተ ተጠያቂዎች ናችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ላለፈው ነገር ሁሉ ይህ ትውልድ ይጠየቅበታል። “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ፤ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን አልፈቀዳችሁም፤ እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል! እላችኋለሁና፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስከምትሉ ድረስ ዳግመኛ አታዩኝም።”
ማቴዎስ 23:23-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦ በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል። ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።
ማቴዎስ 23:23-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፥ ከእንስላል፥ ከከሙን ዐሥራት ትሰጣላችሁ፤ ነገር ግን በሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ነገሮች ትተዋላችሁ፤ እነርሱም ትክክለኛ ፍርድ፥ ምሕረትና ታማኝነት ናቸው፤ ያንን ሳትተዉ ይህንንም ማድረግ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ከምትጠጡትም ሁሉ እንደ ትንኝ ትንሽ የሆነችውን ነገር አጥልላችሁ ትጥላላችሁ፤ እንደ ግመል ትልቅ የሆነውን ነገር ግን ትውጣላችሁ! “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! ብርጭቆውንና ሳሕኑን ከውጪ በኩል ታጠራላችሁ፤ ውስጡ ግን ቅሚያና ሥሥት የሞላበት ነው፤ አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! አስቀድመህ ብርጭቆውንና ሳሕኑን ከውስጥ በኩል አጥራ! በዚያን ጊዜ በውጪም በኩል ንጹሕ ይሆናል። “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! በውስጣቸው በሞቱ ሰዎች አጥንትና በርኩስ ነገር ሁሉ የተሞሉ፥ በውጪ ግን በኖራ ተለስነው የሚያምሩ መቃብሮችን ትመስላላችሁ። እንዲሁም እናንተ፥ በውጪ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ክፋት ሞልቶባችኋል። “እናንተ ግብዞች፥ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር ትገነባላችሁ፤ የጻድቃንንም ሐውልት ታስጌጣላችሁ። ‘በቀድሞ አባቶቻችን ዘመን ተገኝተን ብንሆን ኖሮ የነቢያትን ደም በማፍሰስ ከእነርሱ ጋር ባልተባበርንም ነበር’ ትላላችሁ። እንግዲህ፥ ነቢያትን ለገደሉ ሰዎች ልጆቻቸው መሆናችሁን ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እንግዲያውስ አባቶቻችሁ የጀመሩትን እናንተም ፈጽሙ። እናንተ እባቦች፥ እባብ ልጆች፥ እንዴት ከገሃነም ቅጣት ማምለጥ ትችላላችሁ? ስለዚህ እነሆ፥ እኔ ነቢያትን፥ ጥበበኞችን፥ መምህራንን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹንም በምኲራባችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዱአቸዋላችሁ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም በምድር ላይ ስለ ፈሰሰው የጻድቃን ደም ቅጣቱ በእናንተ ላይ ይደርሳል፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ ቅጣት በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ! ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ፥ እኔም የአንቺን ልጆች በአንድነት ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈቀድኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እንግዲህ እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።”
ማቴዎስ 23:23-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ ምክንያቱም ከአዝሙድ፥ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ታወጣላችሁ፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ፍርድን፥ ምሕረትንና እምነትን ትተዋላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ እነዚህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውራን መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ የጽዋውንና የሳሕኑን ውጭ ታጠራላችሁ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ራስን አለመግዛት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ንጹሕ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውን ውስጡን አጥራ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ በውጫቸው አምረው የሚታዩ በውስጣቸው ግን በሙታን አጥንትና በርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ትመስላላችሁና። እንዲሁም እናንተ በውጭ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ሕገ ወጥነት ሞልቶባችኋል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁ የጻድቃንንም መቃብር ታስጌጣላችሁና፥ ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር’ ትላላችሁ። እንግዲህ የነቢያት ገዳዮች ልጆች መሆናችሁን ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ፈጽሙ። እናንተ እባቦች! የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ እነሆ እኔ ነቢያትን፥ ጥበበኞችና ጻፎችን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ ትሰቅላላችሁም፥ ከእነርሱም አንዳንዶቹን በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዱአቸዋላችሁ፤ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው ጻድቅ ደም ሁሉ በእናንተ ላይ ይደርሳል። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል። “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድዪ ወደ አንቺ የተላኩትንም የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።”