ማቴዎስ 20:29-33
ማቴዎስ 20:29-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ “ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ፥ ማረን” ብለው ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ፥ ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” አለ። “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ” አሉት።
ማቴዎስ 20:29-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። በዚያም ሁለት ዐይነ ስውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው ነበር፤ ኢየሱስም በዚያ ማለፉን ሲሰሙ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” በማለት ጮኹ። ሕዝቡም በግሣጼ ቃል ዝም እንዲሉ ነገሯቸው፤ እነርሱ ግን አምርረው በመጮኽ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” አሉ። ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ” አሉት።
ማቴዎስ 20:29-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና፦ ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ። ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት።
ማቴዎስ 20:29-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተከተሉት። እነሆ፥ በመንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዕውሮች በዚያ በኩል የሚያልፈው ኢየሱስ መሆኑን በሰሙ ጊዜ፥ “ጌታ የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም “ዝም በሉ!” ብለው ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ አድርግልን!” አሉት።
ማቴዎስ 20:29-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከኢያሪኮ ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንደሚያልፍ በሰሙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት።