የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 19:15-30

ማቴዎስ 19:15-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ “መምህር ሆይ! የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ” አለው። እርሱም “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ፤” አለው። እርሱም “የትኞችን?” አለው። ኢየሱስም “አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህንአክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።” ጐበዙም “ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?” አለው። ኢየሱስም “ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ፤” አለው። ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ “እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። ዳግመኛም እላችኋለሁ፤ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል፤” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና “እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል፤” አላቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።

ማቴዎስ 19:15-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ። ከዚያም አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት አገኝ ዘንድ ምን መልካም ነገር ልሥራ” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለግህ ግን ትእዛዞቹን ጠብቅ” አለው። ሰውየውም፣ “የትኞቹን ትእዛዞች?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” ጕልማሳውም ሰው፣ “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” አለው። ኢየሱስም፣ “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ፣ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም ሀብት ታገኛለህ። ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ጕልማሳው ሰውየም ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ደግሜ እላችኋለሁ፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።” ይህን ሲሰሙ፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ በመገረም፣ “እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ። ኢየሱስም እየተመለከታቸው፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፣ “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ በሚመጣው አዲስ ዓለም የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተም የተከተላችሁኝ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ፣ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትፈርዳላችሁ። ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። ነገር ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች፣ ብዙ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።

ማቴዎስ 19:15-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። እርሱም፦ ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው። እርሱም፦ የትኞችን? አለው። ኢየሱስም፦ አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ጕኦበዙም፦ ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጕኦድለኝ ምንድር ነው? አለው። ኢየሱስም፦ ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። ጕኦበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና፦ እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ፦ ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።

ማቴዎስ 19:15-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ አልፎ ሄደ። አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን መልካም ነገር ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ብትፈልግ ግን ትእዛዞችን ፈጽም” አለው። ሰውየውም “የትኞቹን ትእዛዞች?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤ የሚሉት ትእዛዞች ናቸው” አለው። ወጣቱም “እነዚህንማ ትእዛዞች ፈጽሜአለሁ፤ ሌላስ የሚጐድለኝ ምንድን ነው?” አለ። ኢየሱስም “ፍጹም መሆን ብትፈልግ ሂድና ያለህን ሸጠህ ገንዘቡን ለድኻ ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” አለው። ወጣቱ ግን ብዙ ሀብት ስለ ነበረው ይህን በሰማ ጊዜ እየተከዘ ሄደ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ለሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት በጣም ከባድ ነው። ደግሞም እላችኋለሁ፦ ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።” ደቀ መዛሙርቱ ይህን በሰሙ ጊዜ በጣም ተገረሙና “ታዲያ፥ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስ ወደ እነርሱ ተመልክቶ “ይህ ነገር ለሰው የማይቻል ነው፤ ለእግዚአብሔር ግን ሁሉም ይቻለዋል” አለ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ፥ የምናገኘው ምን ይሆን?” አለ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ በክብር ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት በአዲሱ ዓለም የእኔ ተከታዮች የሆናችሁ፥ እናንተም፥ በዐሥራ ሁለት ዙፋኑ ላይ ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ። ስለ እኔ ብሎ ቤቶችን፥ ወይም ወንድሞችን፥ ወይም እኅቶችን፥ ወይም አባትን ወይም እናትን፥ ወይም ልጆችን፥ ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘለዓለም ሕይወትንም ያገኛል። ነገር ግን አሁን ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች ይሆናሉ፤ ኋለኞች የሆኑትም ፊተኞች ይሆናሉ።”

ማቴዎስ 19:15-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እጆቹን ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። እነሆ አንድ ሰው ቀርቦ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ” አለው። እርሱም “ስለ መልካም ነገር እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ከፈልግህ ግን ትእዛዛቱን ጠብቅ፤” አለው። እርሱም “የትኞቹን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ።” ወጣቱም “ይህን ሁሉ ጠብቄአለሁ፤ አሁን የሚጐድለኝ ምንድነው?” አለው። ኢየሱስም “ፍጹም መሆን ከፈለግህ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ በሰማያት መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” አለው። ወጣቱ ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጸጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ከባድ ነው። ደግሜ እላችኋለሁ፤ ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።” ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስ ግን አያቸውና እንዲህ አላቸው “ይህ በሰው ዘንድ የማይቻል ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ የምናገኘው ታዲያ ምንድነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ስለተከተላችሁኝ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በዓሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፥ በዓሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይም ትፈርዳላችሁ። ማንም ስለ ስሜ ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘለዓለም ሕይወትንም ይወርሳል። ነገር ግን ብዙዎቹች ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።