ማቴዎስ 18:21-35
ማቴዎስ 18:21-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም፤ ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ ከአገልጋዮቹ ጋር ሊተሳሰብ የፈለገውን ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡ መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ በብዙ ሺህ መክሊት የሚቈጠር ዕዳ ያለበት አንድ አገልጋይ ተይዞ መጣ። ይህ አገልጋይ ዕዳውን መክፈል ስላልቻለ እርሱም፥ ሚስቱም፥ ልጆቹም፥ ያለውም ንብረት ሁሉ ተሸጦ ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። አገልጋዩ ግን በጌታው እግር ሥር ተንበርክኮ ‘ጌታ ሆይ! እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ!’ ሲል ለመነው። ጌታውም ራራለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት። “ነገር ግን ያ አገልጋይ ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ሳለ መቶ ዲናር ያበደረውን የሥራ ጓደኛውን አገኘና አንገቱን አንቆ ይዞ፥ ‘ያበደርኩህን ገንዘብ ክፈለኝ!’ አለው። አገልጋይ ጓደኛውም በእግሩ ሥር ወድቆ፥ ‘እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ!’ ሲል ለመነው። ሰውየው ግን እምቢ አለው። እንዲያውም ይዞት ሄደና ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወህኒ ቤት አሳሰረው። እንደርሱ ያሉ ሌሎች የሥራ ጓደኞቹ ይህን ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። ጌትዮውም ያን አገልጋይ አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ! ስለ ለመንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ፤ ታዲያ፥ እኔ ዕዳህን እንደ ተውኩልህ፥ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው አገልጋይ ዕዳውን ልትተውለት አይገባህም ነበርን?’ ስለዚህ ጌታው ተቈጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤቱ ኀላፊዎች አሳልፎ ሰጠው። “እንግዲህ እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልብ ይቅር ባትሉ በሰማይ ያለው አባቴም እንዲሁ ያደርግባችኋል።”
ማቴዎስ 18:21-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን?” አለው። ኢየሱስ እንዲህ አለው “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና ‘ጌታ ሆይ! ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ አለው። የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት። ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ‘ዕዳህን ክፈለኝ’ ብሎ ያዘና አነቀው። ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ ‘ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ ብሎ ለመነው። እርሱም አልወደደም፤ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው። ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፤ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ። ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን?’ አለው። ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።”
ማቴዎስ 18:21-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው። “ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ፣ በአገልጋዮቹ እጅ የነበረውን ሒሳብ ለመተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። ሂሳቡን ማጣራት እንደ ጀመረም ዐሥር ሺሕ ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ አገልጋይ አቀረቡለት። አገልጋዩም ያለበትን ዕዳ መክፈል ስላቃተው እርሱ ራሱ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ንብረቱ ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። “በዚህ ጊዜ አገልጋዩ እግሩ ላይ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። ጌታውም ዐዘነለትና ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው። “ያ አገልጋይ ከጌታው ፊት እንደ ወጣ አንድ መቶ ዲናር የእርሱ ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ ዕንቅ አድርጎ በመያዝ፣ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ!’ አለው። “ባልንጀራው አገልጋይም ከፊቱ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው። “ነገር ግን ሊታገሠው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው። የሆነውን ነገር ያዩ ሌሎች አገልጋዮችም በጣም ዐዘኑ፤ ሄደውም ሁኔታውን በሙሉ ለጌታቸው ነገሩት። “በዚህ ጊዜ ጌታው አገልጋዩን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ በቍጣም ያለበትን ዕዳ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው። “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”
ማቴዎስ 18:21-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቍኦጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። መቍኦጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና፦ ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው። የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት። ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና፦ ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው። ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ፦ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው። እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው። ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ። ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ጌታውም ተቍኦጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።
ማቴዎስ 18:21-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ስንት ጊዜ ቢበድለኝ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባርያዎቹ ጋር ሊተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ፥ አስር ሺህ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። መክፈልም ሲያቅተው እርሱ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ያለውም ሁሉ ተሽጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ስለዚህ ባርያው ወድቆ ተንበረከከና ‘እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ አለው። የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት። ነገር ግን ያ ባርያ ከዚያ ወጥቶ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን ከባልንጀሮቹ ባርያዎች አንዱን አገኘና ‘ዕዳህን ክፈለኝ’ ብሎ አንቆ ያዘው። ያል ባልንጀራው ባርያ ወድቆ ‘እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ ብሎ ለመነው። እርሱ ግን አልፈለገም፤ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ሄዶ በወኅኒ አሳሰረው። ባልንጀሮቹ ባርያዎችም ያደረገውን ሁሉ አይተው እጅግ አዘኑ፤ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። ከዚያ በኋላ ጌታው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባርያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ ጌታውም ተቆጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለሚያሠቃዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተም እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ የሰማዩ አባቴ ደግሞ እንዲሁ ያደርግባችኋል።”