የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 16:13-28

ማቴዎስ 16:13-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ ጠየቀ። እነርሱም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው፤” ይላሉ አሉት። እርሱም “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር። ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ! ይህ ከቶ አይደርስብህም፤” ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፤ አንተ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና፥ ዕንቅፋት ሆነህብኛል፤” አለው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።”

ማቴዎስ 16:13-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ፊልጶስ ቂሳርያ ወደተባለው አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለመሆኑ ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። እርሱም፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ብፁዕ ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም። አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም። የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርኸው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታኸው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” ቀጥሎም እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቃቸው። ኢየሱስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ፣ በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር። ጴጥሮስም ኢየሱስን ወደ ጐን ሳብ አድርጎ፣ “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” እያለ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ዘወር ብሎ፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ፤ የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በዐሳብህ ስለሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለው። ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነገር ግን ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው? የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ከመላእክት ጋር ይመጣል፤ ለእያንዳንዱም ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይከፍለዋል። እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት ሰዎች መካከል፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”

ማቴዎስ 16:13-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር። ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ፦ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጕኦድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።

ማቴዎስ 16:13-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ የፊልጶስ ቂሳርያ ወደሚባል ክፍለ ሀገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶች ‘መጥምቁ ዮሐንስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ‘ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ይላሉ” አሉት። ኢየሱስም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። በዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፦ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሰው አይደለም። እኔም እንዲህ እልሃለሁ፤ አንተ (ጴጥሮስ)፥ አለት ነህ፤ በዚህችም የመሠረት ድንጋይ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ ይህችንም ቤተ ክርስቲያን የሞት ኀይል እንኳ አያሸንፋትም። እነሆ፥ ለአንተ የሰማይ መንግሥትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አለብኝ፤ እዚያም ከሽማግሌዎች፥ ከካህናት አለቆችና ከሕግ መምህራን መከራ ይደርስብኛል፤ ይገድሉኛል፤ ግን በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ።” ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን ለብቻ ገለል አድርጎ፦ “ጌታ ሆይ! ከቶ አይሆንም! ይህ ነገር ከቶ አይደርስብህም!” እያለ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዞር ብሎ ጴጥሮስን፦ “አንተ ሰይጣን! ከኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር ስለማታስብ ለእኔ እንቅፋት ነህ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “እኔን መከተል የሚፈልግ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። ሰው የዓለሙን ሁሉ ሀብት ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ፥ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል? የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ሆኖ ከመላእክቱ ጋር ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይከፍለዋል። በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ክብር ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል የማይሞቱ ሰዎች አሉ።”

ማቴዎስ 16:13-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ወደሚባል አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎች ኤልያስ፥ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። እርሱም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይነግሱባትም። የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” ከዚህ በኋላ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት ከሽማግሌዎች፥ ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ብዙ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ጀመር። ጴጥሮስም ገለል አድርጎ ወስዶ “ጌታ ሆይ! ይህ ከቶ አይድረስብህ” ብሎ ይገሥጸው ጀመር። እርሱ ግን ዞሮ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፤ አንተ ሰይጣን! ለእኔ ዕንቅፋት ነህ፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና።” አለው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣልና፤ በዚያን ጊዜ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ እዚህ ከቆሙት መካከል የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”