ማቴዎስ 15:21-31
ማቴዎስ 15:21-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆም ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ “ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል፤” ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት፤” እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም፤” አለ። እርስዋ ግን መጥታ “ጌታ ሆይ! እርዳኝ፤” እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ “የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም፤” አለ። እርስዋም “አዎን ጌታ ሆይ! ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ፤” አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ድዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ በኢየሱስም እግር አጠገብ አስቀመጡአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።
ማቴዎስ 15:21-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አካባቢ ወጥታ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ፤ ራራልኝ፤ ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንድም ቃል አልመለሰላትም፤ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “እየተከተለችን ትጮኻለችና ብታሰናብታትስ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ሆነው ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነው” አለ። ሴትዮዋም እግሩ ላይ ወድቃ፣ “ጌታ ሆይ፤ ርዳኝ” አለች። እርሱም መልሶ፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል አይገባም” አላት። እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከጌታቸው ማእድ የወዳደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ “አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው! እንደ ፈለግሽው ይሁንልሽ” አላት። ልጇም ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወዳለው ስፍራ በመሄድ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ። ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ዐንካሶችን፣ ዐይነ ስውሮችን፣ ሽባዎችን፣ ዲዳዎችን እንዲሁም ሌሎች ብዙዎችን ሕመምተኞች ይዘው ወደ እርሱ በማምጣት በእግሮቹ ሥር አስቀመጧቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳው ሲናገር፣ ሽባው ደኅና ሲሆን፣ ዐንካሳው ቀጥ ብሎ ሲሄድ፣ ዐይነ ስውሩም ሲያይ ተመልክተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ።
ማቴዎስ 15:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።
ማቴዎስ 15:21-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ከተሞች ሄደ፤ ከዚያም አንዲት ከነዓናዊት ሴት ወደ ኢየሱስ መጥታ፥ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ ትሠቃያለችና እባክህ ራራልኝ!” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድም ቃል ሳይመልስላት ዝም አለ፤ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህች ሴት እየተከተለችን ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት!” ሲሉ ለመኑት። እርሱም “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት እንደ በጎች ለጠፉት ብቻ ነው” ሲል መለሰ። ሴትዮዋ ግን ቀርባ በእግሩ ሥር ተንበረከከችና “ጌታ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው። ኢየሱስም “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል የተገባ አይደለም” አለ። እርስዋም “ጌታ ሆይ! እርግጥ ነው፤ ነገር ግን ውሾችም ከጌቶቻቸው ማእድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት እምነትሽ! ትልቅ ነው፤ ስለዚህ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ!” አላት። የሴትዮዋም ልጅ በዚያኑ ሰዓት ዳነች። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራ ላይም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሰዎች አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ድዳዎችንና ሌሎችንም በሽተኞች ይዘው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ በእግሩም ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲድኑ፥ አንካሳዎች በደኅና ሲራመዱ፥ ዕውሮች ሲያዩ በተመለከቱ ጊዜ ተደንቀው የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑ።
ማቴዎስ 15:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አገር መጥታ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ ማረኝ፤ ሴት ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” እያለች ጮኸች። እርሱ ግን አንድ ቃልም አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ከኋላችን እየጮኸች ነውና አሰናብታት” እያሉ ለመኑት። እርሱም “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ነው እንጂ ለሌላ አይደለም” ሲል መለሰ። እርሷ ግን መጥታ እየሰገደች “ጌታ ሆይ! እርዳኝ” አለች። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለቡችሎች መጣል መልካም አይደለም።” እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ! ነገር ግን ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” ሲል መለሰላት። ሴት ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ዲዳዎችን፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፥ በኢየሱስም እግር ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲፈወሱ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።