የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 15:1-9

ማቴዎስ 15:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የኦሪት ሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚሽሩት ለምንድን ነው? ምግብ ሲበሉኮ እጃቸውን አይታጠቡም” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተስ ለወጋችሁ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትሽራላችሁ? እግዚአብሔር፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ይገደል’ ብሎ ሲያዝዝ፣ እናንተ ግን፣ ማንም ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ‘ላደርግላችሁ የሚገባውን ማንኛውንም ነገር ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ’ ቢላቸው፣ ‘አንድ ሰው ይህን ካደረገ ዘንድ አባቱን ወይም እናቱን አክብሯል’ ትላላችሁ። ስለዚህ ለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ። እናንት ግብዞች፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤ “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልኩኛል፣ ትምህርታቸውም የሰው ሥርዐት ነው።’ ”

ማቴዎስ 15:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ፥ ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ “ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ ስለምን ያፈርሳሉ? እነሆ! ምግብ የሚበሉት እጃቸውን ሳይታጠቡ ነው!” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተስ ወጋችሁን ለመጠበቅ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለምን ታፈርሳላችሁ? እግዚአብሔር ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ የስድብ ቃል የተናገረ በሞት ይቀጣል’ ብሎ አዞአል። እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን ‘ከእኔ የምታገኙትን ርዳታ ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ’ ቢላቸው፥ ‘ያ ሰው አባቱን [ወይም እናቱን] ማክበር አያስፈልገውም’ ትላላችሁ፤ ስለዚህ ወጋችሁን ለማጥበቅ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ሕግ ታፈርሳላችሁ፤ እናንተ ግብዞች! ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ሲል የተናገረው ትንቢት ልክ ነው፤ ‘ይህ ሕዝብ በአፉ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ ሰው ሠራሽ ወግና ሥርዓትን፥ እንደ ሕግ አድርጎ እያስተማረ በከንቱ ያመልከኛል።’ ”