ማቴዎስ 13:53-58
ማቴዎስ 13:53-58 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ፥ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።
ማቴዎስ 13:53-58 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች እንደ ጨረሰ፣ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ፤ ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ በምኵራባቸውም ሕዝቡን ያስተምር ጀመር። እነርሱም በመገረም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ታምራት የማድረግ ኀይል ከየት አገኘ? ይህ የዐናጢው ልጅ አይደለምን? የእናቱስ ስም ማርያም አይደለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ከእኛው ጋር አይደሉምን? ታዲያ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” ስለዚህም ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፣ “ነቢይ የማይከበረው በራሱ አገርና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው። ባለ ማመናቸውም ምክንያት ብዙ ታምራትን በዚያ አላደረገም።
ማቴዎስ 13:53-58 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ፦ ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።
ማቴዎስ 13:53-58 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ካበቃ በኋላ፥ ከዚያ ስፍራ ሄደ። ወደ አገሩ ወደ ናዝሬት ከተማ መጥቶ በምኲራቦቻቸው ሕዝብን ያስተምር ነበር፤ የሰሙትም ሁሉ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና ይህን ድንቅ ሥራ ከወዴት አመጣው? ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም የምትባል አይደለችምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር አይደሉምን? ታዲያ፥ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘው?” በዚህም ምክንያት ተሰናክለውበት ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፦ “ነቢይ የማይከበረው በሀገሩና በገዛ ቤቱ ብቻ ነው” አላቸው። ባለማመናቸውም ኢየሱስ በዚያ ብዙ ተአምር አላደረገም።
ማቴዎስ 13:53-58 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም እነዚህን ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ በምኵራባቸው ያስተምራቸው ነበር፥ ተገርመውም እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ኃይል ከየት አገኘው? ይህ የጠራቢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር ያሉ አይደሉምን? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በስተቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። ባለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።