ማቴዎስ 13:18-30
ማቴዎስ 13:18-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፤ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ፤’ አላቸው። ባሮቹም ‘እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን?’ አሉት። እርሱ ግን ‘እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን “እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ፤” እላለሁ’ አለ።”
ማቴዎስ 13:18-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። ነገር ግን ሥር ባለመስደዱ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራን ሰው ይመስላል። በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።” ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም ዐብሮ ብቅ አለ። “የዕርሻው ባለቤት ባሪያዎችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። “እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው። “ባሮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት። “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም ዐብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ዐብረው ይደጉ። በዚያ ጊዜ ዐጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”
ማቴዎስ 13:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው፦ ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም፦ ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም፦ እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን፦ እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን፦ እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።
ማቴዎስ 13:18-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እንግዲህ እናንተ የዘሪው ምሳሌ ምን እንደ ሆነ ስሙ፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ነው፤ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይወስድበታል፤ በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ነው። ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በልቡ ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ስለዚህ በቃሉ ምክንያት አንዳች ችግር ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ቶሎ ይሰናከላል። በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ በማስተዋል የሚቀበለውን ሰው ነው፤ እርሱ ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።” እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘር የዘራውን ሰው ትመስላለች፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ከተኛ በኋላ ጠላት መጣና በስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው አድጎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም በዚያኑ ወቅት ታየ። ስለዚህ የእርሻው ባለቤት አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፥ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ፥ እንክርዳዱ ከወዴት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ይህን ያደረገ ጠላት ነው’ አላቸው። አገልጋዮቹም ‘ታዲያ ሄደን እንክርዳዱን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?’ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው ‘አይሆንም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን አብራችሁ ትነቅላላችሁ። ስለዚህ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ድረስ ስንዴውም እንክርዳዱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜ ዐጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳት እንዲቃጠልም በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን ሰብስቡና በጐተራዬ ክተቱ’ እላቸዋለሁ።”
ማቴዎስ 13:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ በራሱ ሥር የለውም፤ ነገር ግን ለትንሽ ጊዜ ይቆያል፥ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራው፥ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ጭንቀትና የሃብት ማታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ስድሳ አንዱም ሠላሳ ይሰጣል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች። ሰዎቹ ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም ያንጊዜ ታየ። የባለቤቱ ባርያዎችም ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! በእርሻህ ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ’ አላቸው። ባርያዎቹም ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው እንክርዳዱን ስትሰበስቡ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ ተዉአቸው፤ በመከር ጊዜ አጫጆቹን “አስቀድማችሁ እንክርዳዱን በእሳትም ለማቃጠል ሰብስባችሁ በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱት፤ እላቸዋለሁ።”