ማቴዎስ 13:1-12
ማቴዎስ 13:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
ማቴዎስ 13:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቷቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱ ዘር ዐፈሩ ስስ በሆነ፣ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ስስ ስለ ሆነም ፈጥኖ በቀለ። ነገር ግን ፀሓይ ሲመታው ጠወለገ፤ ሥር ባለ መስደዱም ደረቀ። አንዳንዱም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያ ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
ማቴዎስ 13:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው፦ እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
ማቴዎስ 13:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ በባሕር ዳር ቆመው ነበር። ከዚያም በኋላ ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ! አንድ ገበሬ ለመዝራት ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ብዙ ዐፈር ስለሌለበት ጥልቀት አልነበረውም፤ ስለዚህ ዘሩ ወዲያውኑ በቀለ። ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኻማውም ቊጥቋጦ አደገና የዘሩን ቡቃያ አንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
ማቴዎስ 13:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ፥ በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። ብዙ ነገርም በምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። አንዳንዱም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ነገር ግን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። አንዳንዱም በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም በቀለና አነቀው። አንዳንዱም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።