የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 12:7-21

ማቴዎስ 12:7-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

‘ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም፤’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኀጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል፤” አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። ዘረጋትም፤ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው፤ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል “እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም፤ አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

ማቴዎስ 12:7-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሓን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከስሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዷል?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት፣ በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጐትቶ አያወጣውምን? ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዷል” አላቸው። ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላውም እጁ ደኅና ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ። ኢየሱስ ሐሳባቸውን ዐውቆ ከዚያ ዘወር አለ። እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤ ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤ “እነሆ፤ የመረጥሁት፣ የምወድደውና ነፍሴ ደስ የተሠኘችበት ብላቴናዬ፣ መንፈሴን በርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም። ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

ማቴዎስ 12:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና። ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ፦ በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦ እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።

ማቴዎስ 12:7-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደግሞም ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ምን እንደ ሆነ ብታስተውሉ ኖሮ በደል በሌለባቸው ሰዎች ላይ ባልፈረዳችሁም ነበር። እንዲያውም የሰው ልጅ የሰንበትም ጌታ ነው።” ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ምኲራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች “በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው፥ በጉ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ስቦ የማያወጣው ማነው? ታዲያ፥ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እጀ ሽባውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋው ጊዜ እጁ ድኖ ልክ እንደ ደኅነኛው እጅ ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ። ኢየሱስ ግን ሤራቸውን ዐውቆ ከዚያ ቦታ ገለል አለ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሳቸው። ሰዎቹን ግን ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። “እነሆ! የመረጥኩት አገልጋዬ ይህ ነው! እርሱ እኔ የምወደውና የምደሰትበት ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ እርሱም ቅን ፍርድን ለሕዝቦች ያውጃል። እርሱ አይከራከርም ወይም አይጮኽም፤ በመንገዶችም ላይ ድምፁን የሚሰማ የለም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንኳ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጥዋፍ ክር አያጠፋም፤ ይህንንም የሚያደርገው፥ ቅን ፍርድ ድል እስኪነሣ ድረስ ነው። አሕዛብ በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ።”

ማቴዎስ 12:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ ንጹሐኑን ባልኮነናችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ አልፎ ወደ ምኵራባቸው ገባ። እነሆ አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ሊከሱትም ፈልገው “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበት ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ማነው? ታዲያ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።” ከዚያ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋት፤ ያንጊዜ እንደ ሁለተኛዋ ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ተማከሩ። ኢየሱስ ይህንን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው። እንዳያጋልጡትም አዘዛቸው፤ ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “እነሆ የመረጥሁት አገልጋዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያውጃል። አይከራከርም አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ወደ ድል እስኪያመጣ ድረስ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስን የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”