ማቴዎስ 12:1-50

ማቴዎስ 12:1-50 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው “እነሆ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኀጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ‘ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም፤’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኀጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል፤” አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። ዘረጋትም፤ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው፤ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል “እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም፤ አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ድዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው። ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና “እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ሰምተው “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም፤” አሉ። ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤” እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። “ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።” በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን፤” አሉ። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንዱም “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል፤” አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና፤” አለ።

ማቴዎስ 12:1-50 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ ዐለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን እያደረጉ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና ዐብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ፣ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፤ ለካህናት እንጂ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ በላ። ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሓን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከስሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዷል?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት፣ በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጐትቶ አያወጣውምን? ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዷል” አላቸው። ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላውም እጁ ደኅና ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ። ኢየሱስ ሐሳባቸውን ዐውቆ ከዚያ ዘወር አለ። እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤ ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤ “እነሆ፤ የመረጥሁት፣ የምወድደውና ነፍሴ ደስ የተሠኘችበት ብላቴናዬ፣ መንፈሴን በርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም። ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ። ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በምን ሊያስወጧቸው ነው? ስለዚህ ልጆቻችሁ ይፈርዱባችኋል። እኔ ግን አጋንንትን የማስወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች። “ወይስ አንድ ሰው ወደ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ለመዝረፍ ቢፈልግ፣ አስቀድሞ ያን ኀይለኛ ሰው ሳያስር እንዴት አድርጎ ይሳካለታል? ኋላም ቤቱን መበዝበዝ ይችላል። “ከእኔ ጋራ ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋራ የማይሰበስብ ይበትናል። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም። ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም። “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ። እናንተ የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና። መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካም ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር መጥፎ ነገርን ያወጣል። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። ምክንያቱም ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃልና።” ከዚያም አንዳንድ ፈሪሳውያንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋራ ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋራ ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ፣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም በኋላ ሄዶ ከርሱ የከፉ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ። ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”

ማቴዎስ 12:1-50 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው፦ እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና። ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ፦ በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦ እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ። ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው። ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና፦ እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን? አሉ። ፈሪሳውያን ግን ሰምተው፦ ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኵኦነናለህ። በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም፦ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል። ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንዱም፦ እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው። እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦ እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።

ማቴዎስ 12:1-50 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በስንዴ እርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ርቦአቸው ስለ ነበረ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህን አይተው ኢየሱስን “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ!” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር እርሱም ሆነ አብረውት የነበሩት ሰዎች ሊበሉት ያልተፈቀደውን፥ የተቀደሰ ኅብስት በላ። ደግሞስ ካህናት በሰንበት ቀን በቤተ መቅደስ ሰንበትን ሲጥሱ በደል ሆኖ እንደማይቈጠርባቸው በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? ነገር ግን ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እነሆ፥ እዚህ አለ እላችኋለሁ። ደግሞም ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ምን እንደ ሆነ ብታስተውሉ ኖሮ በደል በሌለባቸው ሰዎች ላይ ባልፈረዳችሁም ነበር። እንዲያውም የሰው ልጅ የሰንበትም ጌታ ነው።” ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ምኲራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች “በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው፥ በጉ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ስቦ የማያወጣው ማነው? ታዲያ፥ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እጀ ሽባውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋው ጊዜ እጁ ድኖ ልክ እንደ ደኅነኛው እጅ ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ። ኢየሱስ ግን ሤራቸውን ዐውቆ ከዚያ ቦታ ገለል አለ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሳቸው። ሰዎቹን ግን ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። “እነሆ! የመረጥኩት አገልጋዬ ይህ ነው! እርሱ እኔ የምወደውና የምደሰትበት ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ እርሱም ቅን ፍርድን ለሕዝቦች ያውጃል። እርሱ አይከራከርም ወይም አይጮኽም፤ በመንገዶችም ላይ ድምፁን የሚሰማ የለም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንኳ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጥዋፍ ክር አያጠፋም፤ ይህንንም የሚያደርገው፥ ቅን ፍርድ ድል እስኪነሣ ድረስ ነው። አሕዛብ በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ።” ከዚህ በኋላ ሰዎች አንድ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ድዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ሰውየውም መናገርና ማየት ቻለ። ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው፥ “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “እርሱ ‘ብዔልዜቡል’ በተባለው በአጋንንት አለቃ አማካይነት ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይወድቃል። እንዲሁም አንድ ከተማ ወይም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ ታዲያ፥ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊኖር ይችላል! ደግሞ እኔ አጋንንትን የማስወጣቸው በብዔልዜቡል ከሆነ፥ ልጆቻችሁስ በምን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ ልጆቻችሁ በእናንተ ላይ ይፈርዱባችኋል። እኔ አጋንንትን የማስወጣ በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ ግን እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት በእናንተ ላይ መጥታለች ማለት ነው። ደግሞስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን መዝረፍ እንዴት ይችላል? ኀይለኛውን ካሰረው በኋላ ግን በእርግጥ ንብረቱን ሊዘርፍ ይችላል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። ስለዚህ ሰው የሚያደርገው ማናቸውም ኃጢአት ወይም የስድብ ቃል ሁሉ ይቅር ይባልለታል እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሰው ግን በደሉ ይቅር አይባልለትም። በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ በደሉ ይቅር ይባልለታል። በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም በደሉ ይቅር አይባልለትም። “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ ፍሬውም መልካም ይሆናል፤ ዛፉ መጥፎ ከሆነ ግን ፍሬውም መጥፎ ይሆናል። እናንተ የእባብ ልጆች! ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? ሰው በአፉ የሚናገረው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። “መልካም ሰው ከመልካም መዝገቡ፥ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገቡ ክፉ ነገርን ያወጣል። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰዎች በግዴለሽነት በሚናገሩት በያንዳንዱ ቃል በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። ከቃልህ የተነሣ ይፈረድልሃል፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃል።” በዚያን ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! አንተ ተአምር ስታደርግ ማየት እንፈልጋለን!” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና የማያምን ትውልድ ተአምር ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ተአምር በቀር ሌላ ተአምር አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንዳሳለፈ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ያሳልፋል። የነነዌ ከተማ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ትውልድ ጋር ተነሥተው በእርሱ ላይ ይፈርዱበታል፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት በሰሙ ጊዜ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሓ ገብተዋልና። አሁን ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። የደቡብ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለ መጣች በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ትውልድ ጋር ተነሥታ በእርሱ ላይ ትፈርድበታለች፤ አሁን ግን ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ቦታ ይዞራል። ነገር ግን አያገኝም፤ ስለዚህ ‘ወደ ወጣሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል። ተመልሶም ሲመጣ፥ ቤቱ ባዶ ሆኖ፥ ጸድቶ፥ ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚህ በኋላ፥ ርኩሱ መንፈስ ይሄድና ከእርሱ ይብስ የከፉትን ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል። እነርሱም ቀድሞ የጋኔኑ ቤት ወደ ነበረው ሰው ልብ ገብተው አብረው በዚያ ይኖራሉ። ስለዚህ የዚያ ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድ ላይ የሚሆነው ይህንኑ የመሰለ ነገር ነው።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ገና ሲናገር ሳለ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። [ እዚያ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ኢየሱስን፥ “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጪ ቆመዋል” አለው።] ኢየሱስ ግን “እናቴ ማናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰ። ከዚህ በኋላ እጁን ዘርግቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነሆ፥ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ፥ ወንድሜም፥ እኅቴም፥ እናቴም እርሱ ነው።”

ማቴዎስ 12:1-50 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀመዛሙርቱ ተራቡና እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህንን አይተው “እይ! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ያደርጋሉ፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ካህናት ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት በላ። በሰንበታት በቤተ መቅደስ ያሉ ካህናት ሰንበትን እንደሚያረክሱ ንጹሐንም እንደ ሆኑ በሕጉ አላነበባችሁምን? እላችኋለሁ፥ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ ንጹሐኑን ባልኮነናችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ አልፎ ወደ ምኵራባቸው ገባ። እነሆ አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ሊከሱትም ፈልገው “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበት ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ማነው? ታዲያ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።” ከዚያ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋት፤ ያንጊዜ እንደ ሁለተኛዋ ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ተማከሩ። ኢየሱስ ይህንን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው። እንዳያጋልጡትም አዘዛቸው፤ ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “እነሆ የመረጥሁት አገልጋዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያውጃል። አይከራከርም አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ወደ ድል እስኪያመጣ ድረስ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስን የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።” ከዚህ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ዲዳውም ተናገረ አየም። ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ይህን ሰምተው “ይህ በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። እርሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እርስ በርስዋ የምትከፋፈል መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤ እርስ በርስዋ የምትከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁላ አትቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት መቆም ይችላል? እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆነ፥ ልጆቻችሁ በማን ያስወጡአቸዋል? በዚህም ምክንያት እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማስወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች። ወይስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን እንዴት መዝረፍ ይችላል? ካሰረው በኋላ ግን ቤቱን ይዘርፋል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብ ደግሞ ይበትናል። በዚህም ምክንያት እላችኋለሁ፤ ሰው ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስን የሰደበ ግን አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። “ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ፤ ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከመልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፥ ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህና።” በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁም የሰው ልጅ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። የደቡብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝምም። በዚያን ጊዜ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ሲመጣም ባዶ ሆኖ፥ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ይሄድና ከእርሱ የከፉ ሰባት ሌሎች አጋንንትን ከእርሱ ጋር ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ የሰውየው መጨረሻ ከፊተኛው ይልቅ የከፋ ይሆናል። ለዚህም ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” ለሕዝቡ ይህን እየተናገረ ሳለ፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ እንዲህ አለው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። እጁንም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም እናቴም ነውና።”