የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 10:1-15

ማቴዎስ 10:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥ ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፤ አዘዛቸውም፤ እንዲህም አለ “በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች፤’ ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፤ በከንቱ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል።

ማቴዎስ 10:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣ ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋር ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ። ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደ ሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ። ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ። በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ። ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና። “ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ። ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ። ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ። ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ። እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን በዚያች ከተማ ከሚደርሰው ቅጣት ይልቅ በሰዶምና በገሞራ የሚደርሰው ይቀልላል።

ማቴዎስ 10:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥ ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ፦ በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ። ሄዳችሁም፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል።

ማቴዎስ 10:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያስወጡ፥ በሽታንና ደዌን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ዝርዝር፥ እንደሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ቶማስ፥ ቀራጩ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ቀናኢው ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። አንዱ አስተያየት፥ ከቦታ ወይም ከሀገር ጋር ሲያያይዘው ሌላው ወገን ደግሞ ይሁዳን ውሸታም ወይም አታላይ ብሎ ለመስደብ የተሰጠ ቅጽል ነው ይላል። ኢየሱስ እነዚህን ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ እንደ በጎች ወደ ጠፉት ወደ እስራኤል ሕዝቦች ሂዱ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማይ ቀርባለች!’ እያላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በኪሳችሁ አትያዙ። ለሠራተኛ ምግቡ የሚገባው ስለ ሆነ ለመንገዳችሁ ከረጢት፥ ትርፍ እጀ ጠባብ፥ ትርፍ ጫማ፥ በትርም አትያዙ። በምትገቡበት ከተማ ወይም መንደር፥ ተገቢ የሆነ ሰው ማን እንደ ሆነ መርምሩ፤ ያንንም ስፍራ ለቃችሁ እስክትወጡ ድረስ ከእርሱ ጋር ቈዩ። ወደ ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱ ለሰላማችሁ ተገቢ ቢሆን ሰላማችሁ ይድረሰው፤ ተገቢ ባይሆን ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ማንም ሰው የማይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የማይሰማ ቢሆን ያንን ቤት ወይም ከተማ ለቃችሁ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። በእውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ሰዎች ቅጣቱ ይቀልላቸዋል።

ማቴዎስ 10:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፥ በሽታንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፥ ቶማስና ቀራጩ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፥ ቀናኢው ስምዖንና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸውም፦ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ ወደ ጠፉት በጎች ወደ እስራኤል ቤት ሂዱ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች፤’ ብላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ነሐስ በመቀነታችሁ አትያዙ፥ ለመንገዳችሁ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። በምትገቡባት በማንኛዪቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የተገባው ሰው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ወደ ቤቱም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱ የተገባው ከሆነ ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ይሁን፤ ያልተገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። ማንም የማይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የማይሰማ ከሆነ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉችሁ ውጡ። እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል።