ማቴዎስ 1:17-25
ማቴዎስ 1:17-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፣ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፣ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ልደት ዐሥራ አራት ትውልድ ይሆናል። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። ዕጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለ ነበርና ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ። በዚህ ሐሳብ ሳለ፣ የጌታ መልአክ በሕልም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ ዕጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና።” ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤ “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ይሉታል፤” ትርጕሙም፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ” ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ እንዳዘዘው ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት። ይሁን እንጂ የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም፣ “ኢየሱስ” ብሎ ጠራው።
ማቴዎስ 1:17-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” በነቢይ ከጌታ ዘንድ፥ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፤ ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።
ማቴዎስ 1:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፥ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።
ማቴዎስ 1:17-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎን ምርኮ እስከ መሲሕ ዐሥራ አራት ትውልድ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንዲህ ነበር፦ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች፥ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍ ደግ ሰው ስለ ነበረ፥ ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት አልፈለገም፤ ስለዚህ በስውር ሊተዋት አሰበ። ነገር ግን ይህን ነገር ሲያስብ ሳለ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “የዳዊት ዘር ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ፥ እርስዋን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ። እርስዋ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ስለሚያድን ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ይህም ሁሉ የሆነው ጌታ እንዲህ ሲል በነቢይ አማካይነት የተናገረው እንዲፈጸም ነው፤ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙም ‘ዐማኑኤል’ ተብሎ ይጠራል።” ዐማኑኤል ማለትም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” ማለት ነው። ዮሴፍ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ፥ የጌታ መልአክ ባዘዘው መሠረት እጮኛውን ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት። ይሁን እንጂ፥ ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ አላወቃትም ስሙንም ኢየሱስ ብሎ ጠራው።
ማቴዎስ 1:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ዐሥራ አራት ትውልድ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበር፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ስለ ነበረ ሊያጋልጣት አልፈለገም፥ በስውርም ሊተዋት አሰበ። እርሱ ይህን ሲያስብ ሳለ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርሷ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ይህ ሁሉ የሆነው ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው እንዲፈጸም ነው፦ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” ትርጉሙም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።