ሉቃስ 8:9-17
ሉቃስ 8:9-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ደቀ መዛሙርቱም፥ “ይህቺ ምሳሌ ምንድን ናት?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነዚያ ግን አይተው እንዳያዩ፥ ሰምተውም እንዳይሰሙ፥ እንዳያስተውሉም በምሳሌ ነው። ምሳሌዉም ይህ ነው፤ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ ናቸው፤ አምነውም እንዳይድኑ ሰይጣን መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስድባቸዋል። በጭንጫም ላይ የወደቀው ሰምተው ነገሩን በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር የላቸውም፤ መከራም በአገኛቸው ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቀው ቃሉን ሰምተው የባለጠግነት ዐሳብ፥ የኑሮም መቈርቈር የተድላና የደስታ መጣፈጥም የሚአስጨንቃቸውና ፍሬ የማያፈሩ ናቸው። በመልካም ምድር የወደቀው ግን ቃሉን በበጎና በንጹሕ ልብ የሚሰሙና የሚጠብቁት፥ ታግሠውና ጨክነውም የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትን አብርቶ፥ ዕቃም ከድኖ ከአልጋ በታች የሚያኖራት የለም፤ ነገር ግን የሚመላለሱት ብርሃንን ያዩ ዘንድ በመቅረዝ ላይ ያኖራታል። የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፤ የማይታይም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተከደነ የለም፤
ሉቃስ 8:9-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’ “እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትን አብርቶ በጋን ውስጥ ወይም ከዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና።
ሉቃስ 8:9-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም።
ሉቃስ 8:9-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።” የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀውም ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ለጊዜው ነው፤ ሥር ስለሌላቸውም በፈተና ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ። በእሾኽም ቊጥቋጦ መካከል የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ሐሳብና ሀብት፥ የምድራዊ ኑሮ ምቾትም አንቆ ያለ ፍሬ ያስቀራቸዋል። በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ግን በመልካምና በቅን ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁትን ነው፤ እነርሱ በቃሉ ጸንተው ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መብራት አብርቶ እንቅብ የሚደፋበት ወይም በአልጋ ሥር የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። “እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረ ሳይታወቅ የሚቀር የለም።
ሉቃስ 8:9-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። እንዲሁም በዐለት ላይ ያሉት ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም፥ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቁት እንዲሁ ከእነዚያ ከሰሙት ወገን ናቸው፤ በመንገዳቸውም በዚህ የምድራዊ ሕይወት ምኞትና ሀብት እንዲሁም ምቾት ይታነቃሉ፤ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ ያሉት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በቅን ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፥ በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትንም አብርቶ በእንቅብ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። የማይገለጥ ምንም የተሰወረ የማይታወቅም ወደ ብርሃንም የማይመጣ ምንም የተሸሸገ ነገር የለምና።