ሉቃስ 8:28-38
ሉቃስ 8:28-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስንም ባየው ጊዜ ጮኸ፤ ሮጦም ሰገደለት፤ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ካንተ ጋር ምን አለኝ?” እያለም በታላቅ ቃል ጮኸ፤ እንዳያሠቃየውም ማለደው። ክፉውን ጋኔን ከዚያ ሰው ላይ እንዲወጣ ያዝዘው ነበርና፤ ዘወትርም አእምሮዉን ያሳጣው ነበርና፤ ብላቴኖችም በእግር ብረት አስረው ይጠብቁት ነበር፤ እግር ብረቱንም ይሰብር ነበር፤ ጋኔኑም በምድረ በዳ ያዞረው ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ስምህ ማነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም፥ “ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው፤ ብዙ አጋንንት ይዘውት ነበርና። ወደ ጥልቁም ይገቡ ዘንድ እንዳይሰድዳቸው ማለዱት። በዚያም ብዙ የእሪያ መንጋ በተራራ ላይ ተሰማርቶ ነበር፤ ወደ እሪያዎችም እንዲገቡባቸው ይፈቅድላቸው ዘንድ ማለዱት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። እነዚያ አጋንንትም ከዚያ ሰው ላይ ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፤ የእሪያዎችም መንጋ አብደው ከገደሉ ወደ ባሕር ጠልቀው ሞቱ። እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው ሄዱና ገብተው በከተማዉና በመንደሩ አወሩ። ሰዎችም የሆነውን ያዩ ዘንድ ወጡ፤ ሄደውም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ በደረሱ ጊዜ አጋንንት የወጡለትን ያን ሰው አእምሮዉ ተመልሶለት ልብሱን ለብሶ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። ያዩትም ሰዎች ጋኔን አድሮበት የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ ነገሩአቸው። በጌርጌሴኖንም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከእነርሱ ዘንድ እንዲሄድላቸው ማለዱት፤ ጽኑ ፍርሀት ይዞአቸዋልና፤ ጌታችን ኢየሱስም በታንኳ ሆኖ ተመለሰ። ያም አጋንንት የወጡለት ሰው ከእርሱ ጋር ይሄድ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስን ማለደው፤
ሉቃስ 8:28-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ ፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ጋር ምን ጕዳይ አለህ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ። ርኩሱ መንፈስ ይህን ያለው ከሰውየው እንዲወጣ ኢየሱስ አዝዞት ስለ ነበር ነው። ርኩሱ መንፈስ በየጊዜው ስለሚነሣበት ሰውየው በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ቢጠበቅም፣ የታሰረበትን ሰንሰለት እየበጣጠሰ ያደረበት ጋኔን ወደ በረሓ ይነዳው ነበር። ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው። አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዝዛቸው አጥብቀው ለመኑት። በዚያም አካባቢ በተራራ ወገብ ላይ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሣማው መንጋ ግቡ ብሎ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። አጋንንቱም ከሰውየው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ የዐሣማውም መንጋ በገደሉ አፋፍ ቍልቍል በመንደርደር ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ። እረኞቹም የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ፣ ሸሽተው በመሄድ በከተማውና በገጠሩ አወሩ። ሕዝቡም የተደረገውን ነገር ለማየት ከያሉበት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶ፣ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በኢየሱስም እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ። በአጋንንት የተያዘው ሰው ሲድን ያዩትም፣ እንዴት እንደ ዳነ ለሕዝቡ አወሩላቸው። የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎችም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ስላደረባቸው፣ ከዚያ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ወደ ጀልባው ገብቶ ተመልሶ ሄደ። አጋንንት የወጡለትም ሰው አብሮት ለመሆን ኢየሱስን ለመነው፤ እርሱ ግን እንዲህ ሲል አሰናበተው፤
ሉቃስ 8:28-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም፦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ። ርኵሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ ያዘው ነበርና። ብዙ ዘመንም ይዞት ነበርና፥ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይነዳ ነበር። ኢየሱስም፦ ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና፦ ሌጌዎን አለው። ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት። በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም። አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ። እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት። የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ። አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤
ሉቃስ 8:28-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስን ባየ ጊዜ ጮኸ፤ በኢየሱስ ፊትም ወደቀና ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? እባክህ አታሠቃየኝ፤” አለው። ይህንንም ያለበት ምክንያት ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ከሰውየው እንዲወጣ አዞት ስለ ነበር ነው። ከዚህ በፊት ርኩሱ መንፈስ በሰውየው ላይ ብዙ ጊዜ ይነሣበት ነበር፤ በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ይጠበቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሰንሰለቱን ይበጥስ፥ እግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ጋኔኑም እየነዳ ወደ በረሓ ይወስደው ነበር። ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ብዙ አጋንንት ሰፍረውበት ስለ ነበር “ስሜ ሌጌዎን ነው” ሲል መለሰለት። ወዲያውም አጋንንቱም “እባክህ ወደ ጥልቁ ገደል አትስደደን” ሲሉ ለመኑት። በዚያም ስፍራ በኮረብታ ጥግ የብዙ ዐሣማዎች መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱ “ወደ ዐሣማዎቹ እንድንገባ ፍቀድልን” ሲሉ ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። ስለዚህ አጋንንቱ ከሰውየው ወጥተው በዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹ ከገደሉ ላይ እየተንደረደሩ ወረዱ፤ ወደ ባሕር ገብተውም ሰጠሙ። የዐሣማዎቹም እረኞች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ ሸሽተው ሄዱ፤ በየከተማውና በየገጠሩም ወሬውን አዳረሱ። ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ከየቤታቸው ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ አጋንንት የወጡለትንም ሰው ልቡናው ተመልሶለትና ልብሱንም ለብሶ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ የዐይን ምስክር የነበሩ ሰዎችም አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። ከዚህ በኋላ የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት። ይህንንም ያሉበት ምክንያት በጣም ፈርተው ስለ ነበረ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በጀልባ ተሳፈረና ወደ መጣበት ስፍራ ተመልሶ ሄደ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ኢየሱስን “እባክህ ልከተልህ፤” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ አሰናበተው።
ሉቃስ 8:28-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፦ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? እንዳታሰቃየኝ እለምንሃለሁ፤” አለ። እንዲህም የሆነው ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ አዞት ስለ ነበረ ነው። ለብዙም ጊዜ ይዞት ነበርና፤ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይወሰድ ነበር። ኢየሱስም፦ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና፦ “ሌጌዎን” አለው። ወደ ጥልቁም ሂዱ ብሎ እንዳያዛቸው ለመኑት። በዚያም በኮረብታው ዳርቻ ላይ የብዙ ዐሣማዎች መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ወደ እነርሱም ለመግባት እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም። አጋንንቱም ከሰውዬው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ሐይቁ ተጣድፎ በመውረድ ሰጠመ። እረኞቹም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በገጠሩ አወሩት። ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ፥ ልቡም ተመልሶ፥ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። በጌርጌሴኖንም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ በታላቅ ፍርሃት ተይዘው ስለ ነበር ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ ተመለሰ። አጋንንትም የወጡለት ሰው ከእርሱ ጋር እንዲሆን ለመነው፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ አሰናበተው፦