ሉቃስ 8:1-18
ሉቃስ 8:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ በየከተማዉና በየመንደሩ ተመላለሰ፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት ሰበከላቸው፤ አስተማራቸውም፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ከክፉዎች አጋንንትና ከደዌያቸው ያዳናቸው ሴቶችም አብረውት ነበሩ። እነርሱም፦ መግደላዊት የምትባለው ሰባት አጋንንት የወጡላት ማርያም፥ የሄሮድስ አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናም፥ በገንዘባቸው ያገለግሉት የነበሩ ብዙዎች ሌሎችም ነበሩ። ሕዝቡም ሁሉ፥ ከየከተማዉም ሁሉ ወደ እርሱ የመጡት ሲያዳምጡት እንዲህ ያለ ምሳሌ ነገራቸው። “ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ወደቀና ተረገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። ሌላውም በጭንጫ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ ወዲያው ደረቀ፤ ሥር አልነበረውምና። ሌላዉም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ አደገና አነቀው። በመልካም መሬት ላይ የወደቀ ዘርም ነበረ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንም ብሎ፥ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፥ “ይህቺ ምሳሌ ምንድን ናት?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነዚያ ግን አይተው እንዳያዩ፥ ሰምተውም እንዳይሰሙ፥ እንዳያስተውሉም በምሳሌ ነው። ምሳሌዉም ይህ ነው፤ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ ናቸው፤ አምነውም እንዳይድኑ ሰይጣን መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስድባቸዋል። በጭንጫም ላይ የወደቀው ሰምተው ነገሩን በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር የላቸውም፤ መከራም በአገኛቸው ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቀው ቃሉን ሰምተው የባለጠግነት ዐሳብ፥ የኑሮም መቈርቈር የተድላና የደስታ መጣፈጥም የሚአስጨንቃቸውና ፍሬ የማያፈሩ ናቸው። በመልካም ምድር የወደቀው ግን ቃሉን በበጎና በንጹሕ ልብ የሚሰሙና የሚጠብቁት፥ ታግሠውና ጨክነውም የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትን አብርቶ፥ ዕቃም ከድኖ ከአልጋ በታች የሚያኖራት የለም፤ ነገር ግን የሚመላለሱት ብርሃንን ያዩ ዘንድ በመቅረዝ ላይ ያኖራታል። የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፤ የማይታይም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተከደነ የለም፤ እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ አስተውሉ፤ ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
ሉቃስ 8:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ ዐለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣ የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ። ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።” ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’ “እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና። እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
ሉቃስ 8:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤ አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥ የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር። ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት። ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ፦ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።
ሉቃስ 8:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየከተማውና በየመንደሩ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከና የምሥራች እያበሠረ ያልፍ ነበር፤ ዐሥራ ሁለቱም አብረውት ነበሩ። እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስት የተላቀቁና ከበሽታ የተፈወሱ ሴቶች ኢየሱስን ይከተሉት ነበር፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፥ የሄሮድስ ቤት አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን በገንዘባቸው ያገለግሉ ነበር። ብዙ ሕዝብ ከየከተማው ወደ እርሱ መጥተው በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፤ ወፎችም በሉት። ሌላውም ዘር በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መሬቱ እርጥበት ስላልነበረው ቡቃያው ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹ አብሮ አደገና አንቆ አስቀረው። ሌላው ዘር ግን በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ እያንዳንዱ መቶ እጥፍ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።” የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀውም ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ለጊዜው ነው፤ ሥር ስለሌላቸውም በፈተና ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ። በእሾኽም ቊጥቋጦ መካከል የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ሐሳብና ሀብት፥ የምድራዊ ኑሮ ምቾትም አንቆ ያለ ፍሬ ያስቀራቸዋል። በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ግን በመልካምና በቅን ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁትን ነው፤ እነርሱ በቃሉ ጸንተው ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መብራት አብርቶ እንቅብ የሚደፋበት ወይም በአልጋ ሥር የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። “እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረ ሳይታወቅ የሚቀር የለም። “ስለዚህ ቃሉን እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ሰው ተጨምሮ ይሰጠዋል፤ የሌለው ግን አለኝ ብሎ የሚያስበው እንኳ ይወሰድበታል።”
ሉቃስ 8:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እያበሠረ በየከተማውና በየመንደሩ ያልፍ ነበር፤ ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ ከእነርሱም፦ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥ የሄሮድስ መጋቢ የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ብዙዎች ሌሎችም ሆነው ከንብረታቸው በመጠቀም ያገለግሉአቸው ነበር። ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበና ከየከተማውም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦ “ዘሪ ዘሩን ለመዝራት ወጣ። በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ተረገጠም፤ የሰማይ ወፎችም ጨረሱት። ሌላውም በዐለት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንንም እየተናገረ፦ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፤” ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። እንዲሁም በዐለት ላይ ያሉት ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም፥ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ ይክዳሉ። በእሾህም መካከል የወደቁት እንዲሁ ከእነዚያ ከሰሙት ወገን ናቸው፤ በመንገዳቸውም በዚህ የምድራዊ ሕይወት ምኞትና ሀብት እንዲሁም ምቾት ይታነቃሉ፤ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ ያሉት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በቅን ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፥ በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትንም አብርቶ በእንቅብ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። የማይገለጥ ምንም የተሰወረ የማይታወቅም ወደ ብርሃንም የማይመጣ ምንም የተሸሸገ ነገር የለምና። ስለዚህ እንዴት እንደምትሰሙ በጥንቃቄ አጢኑ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”