ሉቃስ 6:20-36

ሉቃስ 6:20-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እር​ሱም ወደ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ዐይ​ኖ​ቹን አን​ሥቶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንተ ድሆች፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት የእ​ና​ንተ ናትና። ዛሬ የም​ት​ራቡ፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ ትጠ​ግ​ባ​ላ​ች​ሁና፤ ዛሬ የም​ታ​ለ​ቅሱ፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ ትስ​ቃ​ላ​ች​ሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠ​ሉ​አ​ችሁ፥ ከሰው ለይ​ተው ቢአ​ሳ​ድ​ዱ​አ​ችሁ፥ ቢሰ​ድ​ቡ​አ​ችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአ​ወ​ጡ​ላ​ችሁ ብፁ​ዓን ናችሁ። ያን​ጊዜ ደስ ይበ​ላ​ችሁ፤ በደ​ስ​ታም ዝለሉ፤ ዋጋ​ችሁ በሰ​ማይ ብዙ ነውና፤ አባ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም ነቢ​ያ​ትን እን​ዲሁ አድ​ር​ገ​ዋ​ቸው ነበ​ርና። ነገር ግን እና​ንተ ባለ​ጠ​ጎች፥ ወዮ​ላ​ችሁ፥ ደስ​ታ​ች​ሁን ጨር​ሳ​ች​ኋ​ልና። ዛሬ ለም​ት​ጠ​ግቡ፥ ወዮ​ላ​ችሁ፥ ትራ​ባ​ላ​ች​ሁና፤ ዛሬ ለም​ት​ስ​ቁም ወዮ​ላ​ችሁ፥ ታዝ​ና​ላ​ች​ሁና፤ ታለ​ቅ​ሳ​ላ​ች​ሁ​ምና። ሰዎች ሁሉ ስለ እና​ንተ መል​ካ​ሙን ነገር ቢና​ገ​ሩ​ላ​ችሁ ወዮ​ላ​ችሁ፥ አባ​ቶ​ቻ​ቸው ለሐ​ሰ​ተ​ኞች ነቢ​ያት እን​ዲህ ያደ​ርጉ ነበ​ርና። “ለም​ት​ሰ​ሙኝ ለእ​ና​ንተ ግን እን​ዲህ እላ​ች​ኋ​ለሁ፦ ጠላ​ቶ​ቻ​ች​ሁን ውደዱ፤ ለሚ​ጠ​ሉ​አ​ች​ሁም መል​ካም አድ​ርጉ። የሚ​ረ​ግ​ሙ​አ​ች​ሁን መር​ቁ​አ​ቸው፤ ለሚ​በ​ድ​ሉ​አ​ች​ሁም ጸል​ዩ​ላ​ቸው። ጕን​ጭ​ህን ለሚ​መ​ታ​ህም ሁለ​ተ​ኛ​ይ​ቱን ስጠው፤ መጐ​ና​ጸ​ፊ​ያ​ህን ለሚ​ወ​ስ​ድም ቀሚ​ስ​ህን ደግሞ አት​ከ​ል​ክ​ለው። ለሚ​ለ​ም​ን​ህም ሁሉ ስጥ፤ ገን​ዘ​ብ​ህን የሚ​ወ​ስ​ደ​ው​ንም እን​ዲ​መ​ልስ አት​ጠ​ይ​ቀው። ሰዎች ሊያ​ደ​ር​ጉ​ላ​ችሁ እን​ደ​ም​ት​ወ​ዱ​ትም እን​ዲሁ እና​ንተ አድ​ር​ጉ​ላ​ቸው። የሚ​ወ​ድ​ዱ​አ​ች​ሁን ብቻ ብት​ወ​ዱማ እን​ግ​ዲህ ዋጋ​ችሁ ምን​ድን ነው? ይህ​ንስ ኃጥ​ኣ​ንም ያደ​ር​ጋሉ፤ የሚ​ወ​ድ​ዳ​ቸ​ው​ንም ይወ​ድ​ዳሉ። በጎ ለሚ​ያ​ደ​ር​ጉ​ላ​ችሁ በጎ ብታ​ደ​ርጉ እን​ግ​ዲህ ዋጋ​ችሁ ምን​ድን ነው? እን​ዲ​ህስ ኃጥ​ኣ​ንም ያደ​ር​ጋሉ። እን​ዲ​ከ​ፍ​ላ​ችሁ ተስፋ ለም​ታ​ደ​ር​ጉት ብታ​በ​ድሩ እን​ግ​ዲህ ዋጋ​ችሁ ምን​ድን ነው? ኃጥ​ኣ​ንም በአ​በ​ደ​ሩት ልክ ይከ​ፍ​ሉ​አ​ቸው ዘንድ ለኃ​ጥ​ኣን ያበ​ድ​ራ​ሉና። አሁ​ንም ጠላ​ቶ​ቻ​ች​ሁን ውደዱ፤ መል​ካ​ምም አድ​ር​ጉ​ላ​ቸው፤ እን​ዲ​መ​ል​ሱ​ላ​ችሁ ተስፋ ሳታ​ደ​ርጉ አበ​ድሩ፤ ዋጋ​ች​ሁም ብዙ ይሆ​ናል፤ የል​ዑ​ልም ልጆች ትሆ​ና​ላ​ችሁ፤ እርሱ ለበ​ጎ​ዎ​ችና ለክ​ፉ​ዎች ቸር ነውና። ሰማ​ያዊ አባ​ታ​ችሁ የሚ​ራራ እንደ ሆነ እና​ን​ተም የም​ት​ራሩ ሁኑ።

ሉቃስ 6:20-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንተ ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤ እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤ ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣ ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣ ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ። “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያ ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና። “ነገር ግን እናንተ ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናናታችሁን አሁኑኑ ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትሥቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁ፤ ታለቅሳላችሁም። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ። አንዱን ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህን አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድ እንዲመልስልህ አትጠይቀው። ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው። “የሚወድዷችሁን ብቻ ብትወድዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወድዷቸውን ይወድዳሉና። መልካም ላደረጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ እንደዚያ ያደርጋሉና። ብድር ይመልሳል ለምትሉት ብታበድሩ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ያበደሩትን ያህል መልሰው ለመቀበል ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ።

ሉቃስ 6:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና። ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና። እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።

ሉቃስ 6:20-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤ “በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ! በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር። “እናንተ ሀብታሞች ግን ለምቾታችሁ የሚሆነውን ሁሉ አሁን አግኝታችኋልና ወዮላችሁ! “እናንተ አሁን የጠገባችሁ፥ ኋላ ትራባላችሁና ወዮላችሁ! እናንተ አሁን የምትስቁ፥ ኋላ ስለምታዝኑና ስለምታለቅሱ ወዮላችሁ! “ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር። “ለእናንተ ለምትሰሙኝ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም ነገር አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው፤ አንዱን ጒንጭህን በጥፊ ለሚመታህ፥ ሌላውንም ጒንጭህን እንዲመታ አዙርለት፤ ነጠላህን ለሚወስድብህ፥ እጀ ጠባብህንም ጨምረህ ስጠው፤ ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም የሚወዱአቸውን ይወዳሉ፤ መልካም ነገር ለሚያደርጉላችሁ እናንተም መልካም ነገር ብታደርጉላቸው ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ ‘ይመልሱልናል’ ብላችሁ ለምታስቡአቸው ሰዎች ብታበድሩ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ? ያንኑ ያበደሩትን መልሰው ለመቀበልማ ኃጢአተኞችም ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ! መልካም ነገርም አድርጉላቸው፤ ‘ብድራችን ይመለስልናል’ ብላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ይህን ብታደርጉ ዋጋችሁ ትልቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጆችም ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለውለታ ቢሶችና ለክፉዎች እንኳ ሳይቀር ቸር ነው። የሰማይ አባታችሁ መሓሪ እንደ ሆነ እናንተም እንዲሁ መሓሪዎች ሁኑ።

ሉቃስ 6:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁና ሲነቅፉአችሁ፥ በክፉም ስማችሁን ሲያጠፉ ብፁዓን ናችሁ! እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ በዚያን ቀን ተደሰቱ፤ በደስታም ዝለሉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ! መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ! ታዝናላችሁ እንባንም ታፈሳላችሁና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉ ነበርና። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፤ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን እንኳ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህንም የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። እንዲሁም ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትወድዱትን ነገር እናንተ ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ያን ያደርጋሉና። ልትቀበሉአቸው ተስፋ የምታደርጉአቸውን ሰዎች ብታበድሩ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ባበደሩት ዋጋ ልክ እንዲመለስላቸው ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉ፤ ይመለስልናልም ብላችሁ ምንም ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።