ሉቃስ 6:12-19
ሉቃስ 6:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፣ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ። ኢየሱስም አብሯቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፤ እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።
ሉቃስ 6:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፤ ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ከውስጣቸውም ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው። እነርሱም እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ። ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናዒ የሚባለው ስምዖን። የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ የከዳውና አሳልፎ የሰጠው ያስቆሮቱ ሰው ይሁዳም ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሰፊ ቦታ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከመላው ይሁዳና ከኢየሩሳሌም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርቻ ትምህርቱን ሊሰሙ፥ ከደዌአቸውም ሊፈወሱ የመጡት ከሕዝቡ ወገን እጅግ ብዙዎች ነበሩ። ክፉዎች አጋንንት ያደሩባቸውም ይፈወሱ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር፤ ኀይል ከእርሱ ይወጣ ነበርና፥ ሁሉንም ይፈውሳቸው ነበር።
ሉቃስ 6:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።
ሉቃስ 6:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፤ እዚያ ሌሊቱን ሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእነርሱም መካከል ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም ቀጥለው የሚገኙት ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና “ቀናተኛ” ተብሎ የሚጠራው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮታዊው ይሁዳ። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር። በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር። የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።
ሉቃስ 6:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በነዚህም ወራት ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፤ ከእነርሱም ዐሥራ ሁለት መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው፤ እነርሱም፦ ጴጥሮስ ብሎ እንደገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስም፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስንና ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናተኛ የተባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ከሐዲ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳም ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሜዳማ ስፍራ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ እንዲሁም ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም እጅግ ብዙ ሰዎች እርሱን ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ የመጡ ነበሩ፤ በርኩሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ሰዎች ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።