ሉቃስ 6:1-26

ሉቃስ 6:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚ​ህም በኋላ ደግሞ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በሰ​ን​በት ቀን በእ​ርሻ መካ​ከል ሄደ፤ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም እሸት ቈር​ጠው በእ​ጃ​ቸው እያሹ በሉ። ፈሪ​ሳ​ው​ያ​ንም፥ “በሰ​ን​በት ሊደ​ረግ የማ​ይ​ገ​ባ​ውን ለምን ታደ​ር​ጋ​ላ​ችሁ?” አሉ​አ​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እር​ሱና ከእ​ርሱ ጋር የነ​በ​ሩ​ትም በተ​ራቡ ጊዜ ዳዊት ያደ​ረ​ገ​ውን አላ​ነ​በ​ባ​ች​ሁ​ምን? ወደ ቤተ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ገባ፥ ከካ​ህ​ና​ቱም ብቻ በቀር ሊበ​ሉት የማ​ይ​ገ​ባ​ውን የመ​ሥ​ዋ​ዕ​ቱን ኅብ​ስት ወስዶ እንደ በላ፥ አብ​ረ​ውት ለነ​በ​ሩ​ትም እንደ ሰጣ​ቸው አላ​ነ​በ​ባ​ች​ሁ​ምን? የሰው ልጅ ለሰ​ን​በት ጌታዋ ነው” አላ​ቸው። ከዚ​ህም በኋላ በሌ​ላ​ይቱ ሰን​በት ወደ ምኵ​ራቡ ገባና አስ​ተ​ማ​ራ​ቸው፤ በዚ​ያም ቀኝ እጁ የሰ​ለ​ለች ሰው ነበረ። ጻፎ​ችና ፈሪ​ሳ​ው​ያ​ንም የሚ​ከ​ሱ​በት ምክ​ን​ያት ያገኙ ዘንድ፥ በሰ​ን​በት ይፈ​ው​ሰው እንደ ሆነ ብለው ይጠ​ባ​በ​ቁት ነበር። እርሱ ግን ዐሳ​ባ​ቸ​ውን ያው​ቅ​ባ​ቸው ነበ​ርና እጁ የሰ​ለ​ለ​ች​ውን ሰው፥ “ተነ​ሥ​ተህ በመ​ካ​ከል ቁም” አለው፤ ተነ​ሥ​ቶም ቆመ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እጠ​ይ​ቃ​ች​ኋ​ለሁ፤ በሰ​ን​በት ሊደ​ረግ የሚ​ገ​ባው ምን​ድ​ነው? መል​ካም መሥ​ራት ነውን? ወይስ ክፉ መሥ​ራት? ነፍ​ስን ማዳን ነውን? ወይስ መግ​ደል?” እነ​ር​ሱም ዝም አሉ፤ ወደ እነ​ር​ሱም ዙሮ ከተ​መ​ለ​ከተ በኋላ፦ ያን ሰው፥ “እጅ​ህን ዘርጋ” አለው፤ ሰው​ዬ​ውም ዘረ​ጋት፤ እጁም ዳነ​ችና እንደ ሁለ​ተ​ኛ​ይቱ ሆነች። እነ​ርሱ ግን፥ እጅግ ተቈጡ፤ በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱ​ስም ምን እን​ድ​ሚ​ያ​ደ​ር​ጉ​በት እርስ በር​ሳ​ቸው ተማ​ከሩ። በዚ​ያም ወራት ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ሊጸ​ልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊ​ቱን ሁሉ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይጸ​ልይ ነበር፤ ሲነ​ጋም ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱን ወደ እርሱ ጠራ​ቸው፤ ከው​ስ​ጣ​ቸ​ውም ዐሥራ ሁለ​ቱን መረጠ፤ ሐዋ​ር​ያት ብሎም ሰየ​ማ​ቸው። እነ​ር​ሱም እነ​ዚህ ናቸው፦ ጴጥ​ሮስ የተ​ባ​ለው ስም​ዖን፥ ወን​ድ​ሙም እን​ድ​ር​ያስ፥ ያዕ​ቆ​ብና ዮሐ​ንስ፥ ፊል​ጶ​ስና በር​ተ​ሎ​ሜ​ዎስ። ማቴ​ዎ​ስና ቶማስ፥ የእ​ል​ፍ​ዮስ ልጅ ያዕ​ቆ​ብና ቀናዒ የሚ​ባ​ለው ስም​ዖን። የያ​ዕ​ቆብ ወን​ድም ይሁዳ፥ የከ​ዳ​ውና አሳ​ልፎ የሰ​ጠው ያስ​ቆ​ሮቱ ሰው ይሁ​ዳም ናቸው። ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ወርዶ በሰፊ ቦታ ቆመ፤ ከደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ወገን ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከመ​ላው ይሁ​ዳና ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም፥ ከጢ​ሮ​ስና ከሲ​ዶና ባሕር ዳርቻ ትም​ህ​ር​ቱን ሊሰሙ፥ ከደ​ዌ​አ​ቸ​ውም ሊፈ​ወሱ የመ​ጡት ከሕ​ዝቡ ወገን እጅግ ብዙ​ዎች ነበሩ። ክፉ​ዎች አጋ​ን​ንት ያደ​ሩ​ባ​ቸ​ውም ይፈ​ወሱ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ ሊዳ​ስ​ሱት ይሹ ነበር፤ ኀይል ከእ​ርሱ ይወጣ ነበ​ርና፥ ሁሉ​ንም ይፈ​ው​ሳ​ቸው ነበር። እር​ሱም ወደ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ዐይ​ኖ​ቹን አን​ሥቶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንተ ድሆች፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት የእ​ና​ንተ ናትና። ዛሬ የም​ት​ራቡ፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ ትጠ​ግ​ባ​ላ​ች​ሁና፤ ዛሬ የም​ታ​ለ​ቅሱ፥ ብፁ​ዓን ናችሁ፤ ትስ​ቃ​ላ​ች​ሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠ​ሉ​አ​ችሁ፥ ከሰው ለይ​ተው ቢአ​ሳ​ድ​ዱ​አ​ችሁ፥ ቢሰ​ድ​ቡ​አ​ችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአ​ወ​ጡ​ላ​ችሁ ብፁ​ዓን ናችሁ። ያን​ጊዜ ደስ ይበ​ላ​ችሁ፤ በደ​ስ​ታም ዝለሉ፤ ዋጋ​ችሁ በሰ​ማይ ብዙ ነውና፤ አባ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም ነቢ​ያ​ትን እን​ዲሁ አድ​ር​ገ​ዋ​ቸው ነበ​ርና። ነገር ግን እና​ንተ ባለ​ጠ​ጎች፥ ወዮ​ላ​ችሁ፥ ደስ​ታ​ች​ሁን ጨር​ሳ​ች​ኋ​ልና። ዛሬ ለም​ት​ጠ​ግቡ፥ ወዮ​ላ​ችሁ፥ ትራ​ባ​ላ​ች​ሁና፤ ዛሬ ለም​ት​ስ​ቁም ወዮ​ላ​ችሁ፥ ታዝ​ና​ላ​ች​ሁና፤ ታለ​ቅ​ሳ​ላ​ች​ሁ​ምና። ሰዎች ሁሉ ስለ እና​ንተ መል​ካ​ሙን ነገር ቢና​ገ​ሩ​ላ​ችሁ ወዮ​ላ​ችሁ፥ አባ​ቶ​ቻ​ቸው ለሐ​ሰ​ተ​ኞች ነቢ​ያት እን​ዲህ ያደ​ርጉ ነበ​ርና።

ሉቃስ 6:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋራ ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው። በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከስሱት ምክንያት በመፈለግ፣ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለችበትን ሰው፣ “ተነሥተህ መካከል ላይ ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም፣ “እስኪ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን በቍጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ። ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስም ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጥቶ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀነናዊው የተባለው ስምዖን፣ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ። ኢየሱስም ዐብሯቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፤ እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ ኀይል ከርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንተ ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤ እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤ ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣ ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣ ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ። “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያ ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና። “ነገር ግን እናንተ ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናናታችሁን አሁኑኑ ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትሥቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁ፤ ታለቅሳላችሁም። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና።

ሉቃስ 6:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ፦ በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው። ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ፦ ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም። በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው፦ ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ። በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።

ሉቃስ 6:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ በእጃቸው ማሸትና መብላት ጀመሩ፤ ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርቱን “በሰንበት ቀን ሊደረግ የማይገባውን ነገር ስለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እርሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ የመባ ኅብስት አንሥቶ በላ፤ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው፤” አላቸው። በሌላም ሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ እዚያም ቀኝ እጁ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ወንጀል ለማግኘት ፈልገው፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እጀ ሽባውን “ተነሥና በመካከል ቁም!” አለው፤ ሽባውም ተነሣና በመካከል ቆመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን? ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ኢየሱስ በዙሪያው ወዳሉት ሰዎች ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እጀ ሽባውን፥ “እጅህን ዘርጋ!” አለው። እርሱም እጁን በዘረጋው ጊዜ ዳነለትና እንደ ሌላው እጅ ደኅና ሆነ። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ግን በጣም ተቈጥተው በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ። አንድ ቀን ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፤ እዚያ ሌሊቱን ሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእነርሱም መካከል ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም ቀጥለው የሚገኙት ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና “ቀናተኛ” ተብሎ የሚጠራው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮታዊው ይሁዳ። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር። በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር። የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤ “በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ! በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር። “እናንተ ሀብታሞች ግን ለምቾታችሁ የሚሆነውን ሁሉ አሁን አግኝታችኋልና ወዮላችሁ! “እናንተ አሁን የጠገባችሁ፥ ኋላ ትራባላችሁና ወዮላችሁ! እናንተ አሁን የምትስቁ፥ ኋላ ስለምታዝኑና ስለምታለቅሱ ወዮላችሁ! “ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር።

ሉቃስ 6:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እነሆ፥ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ስለምን ታደርጋላችሁ?” ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ እንዲህ አለ፦ “ዳዊት በተራበ ጊዜ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን ነገር አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር ለመብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን ኅብስት ወስዶ እንዴት እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንዴት እንደሰጣቸው ይገልጥ የለምን?” እርሱም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤” አላቸው። እነሆ በሌላ ሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከስሱበትን ምክንያት ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፦ “ተነሣና በመካከል ቁም፤” አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነውን ወይንስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ነውን ወይንስ ማጥፋት?” በዙርያው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ከቃኘ በኋላ ሰውዬውን፦ “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። እርሱም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ደኅና ሆነ። እነርሱ ግን በቁጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስም ላይ ምን እንደሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። በነዚህም ወራት ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፤ ከእነርሱም ዐሥራ ሁለት መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው፤ እነርሱም፦ ጴጥሮስ ብሎ እንደገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስም፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስንና ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናተኛ የተባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ከሐዲ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳም ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሜዳማ ስፍራ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ እንዲሁም ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም እጅግ ብዙ ሰዎች እርሱን ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ የመጡ ነበሩ፤ በርኩሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ሰዎች ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁና ሲነቅፉአችሁ፥ በክፉም ስማችሁን ሲያጠፉ ብፁዓን ናችሁ! እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ በዚያን ቀን ተደሰቱ፤ በደስታም ዝለሉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ! መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ! ታዝናላችሁ እንባንም ታፈሳላችሁና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉ ነበርና።