ሉቃስ 4:33-44

ሉቃስ 4:33-44 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በም​ኵ​ራ​ብም ርኩስ መን​ፈስ የያ​ዘው አንድ ሰው ነበር፤ በታ​ላቅ ቃልም ጮኾ፦ “የና​ዝ​ሬቱ ኢየ​ሱስ ሆይ፥ ከአ​ንተ ጋር ምን አለን? ያለ​ጊ​ዜ​አ​ችን ልታ​ጠ​ፋን መጣ​ህን? የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቅዱስ ሆይ፥ አንተ ማን እን​ደ​ሆ​ንህ ዐው​ቅ​ሃ​ለሁ” አለ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ዝም በልና ከእ​ርሱ ውጣ” ብሎ ገሠ​ጸው፤ ጋኔ​ኑም በም​ኵ​ራቡ መካ​ከል ጣለ​ውና ከእ​ርሱ ወጣ፤ ነገር ግን ምንም አል​ጐ​ዳ​ውም። ሁሉም ደነ​ገጡ፤ እርስ በር​ሳ​ቸ​ውም ተነ​ጋ​ገሩ፤ እን​ዲ​ህም አሉ፥ “ይህ ነገር ምን​ድን ነው? ክፉ​ዎ​ችን አጋ​ን​ንት በሥ​ል​ጣ​ንና በኀ​ይል ያዝ​ዛ​ቸ​ዋ​ልና፥ እነ​ር​ሱም ይወ​ጣ​ሉና።” ዝና​ውም በዙ​ሪ​ያዉ ባሉ መን​ደ​ሮች ሁሉ ወጣ፤ ተሰ​ማም። ከም​ኵ​ራ​ቡም ወጥቶ ወደ ስም​ዖን ቤት ገባ፤ የስ​ም​ዖን አማ​ትም በብ​ርቱ ንዳድ ታማ ነበ​ርና ስለ እር​ስዋ ነገ​ሩት። በአ​ጠ​ገ​ብ​ዋም ቁሞ ንዳ​ድ​ዋን ገሠ​ጸ​ውና ተዋት፤ ወዲ​ያ​ውም ተነ​ሥታ አገ​ለ​ገ​ለ​ቻ​ቸው። ፀሐ​ይም በገባ ጊዜ ልዩ ልዩ ደዌ ያለ​ባ​ቸ​ውን ድው​ያን ሁሉ አመ​ጡ​ለት፤ ከእ​ነ​ር​ሱም በእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ ላይ እጁን ጭኖ ፈወ​ሳ​ቸው። ብዙ አጋ​ን​ን​ትም፥ “አንተ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ክር​ስ​ቶስ ነህ” እያ​ሉና እየ​ጮሁ ይወጡ ነበር፤ እር​ሱም ይገ​ሥ​ጻ​ቸው ነበር፤ ክር​ስ​ቶ​ስም እንደ ሆነ ያውቁ ነበ​ርና እን​ዲ​ና​ገሩ አይ​ፈ​ቅ​ድ​ላ​ቸ​ውም ነበር። በነጋ ጊዜም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝ​ቡም እየ​ፈ​ለ​ጉት ወደ እርሱ ሄዱ፤ አል​ፎ​አ​ቸው እን​ዳ​ይ​ሄ​ድም አቆ​ሙት። እርሱ ግን፥ “ስለ​ዚህ ተል​ኬ​አ​ለ​ሁና ለሌ​ሎች ከተ​ሞች ደግሞ ስለ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት ወን​ጌል እነ​ግ​ራ​ቸው ዘንድ ይገ​ባ​ኛል” አላ​ቸው። በገ​ሊላ ምኲ​ራ​ቦ​ችም ይሰ​ብክ ነበር።

ሉቃስ 4:33-44 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ እርሱም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኾ፣ “ወዮ! የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ምን የሚያገናኘን ጕዳይ አለ? የመጣኸው ልታጠፋን ነውን? አንተ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” አለው። ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጣለውና ምንም ጕዳት ሳያደርስበት ለቅቆት ከርሱ ወጣ። ሁሉም ተገረሙ፤ እርስ በርሳቸውም፣ “ለመሆኑ ይህ ትምህርት ምንድን ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም እኮ ይወጣሉ” ተባባሉ። የእርሱም ዝና በአካባቢው ወዳለው ስፍራ ሁሉ ወጣ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከምኵራብ ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም ዐማት ኀይለኛ ትኵሳት ይዟት ታምማ ነበር፤ እንዲፈውሳትም ስለ እርሷ ለመኑት። እርሱም ወደ ተኛችበት ጠጋ ብሎ በማጐንበስ ትኵሳቱን ገሠጸው፤ ትኵሳቱም ለቀቃትና ወዲያው ተነሥታ አስተናገደቻቸው። ፀሓይ መጥለቂያ ላይም፣ የተለያየ ሕመም ያደረባቸውን ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። አጋንንትም ደግሞ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉና እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ። እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ ክርስቶስ መሆኑንም ያውቁ ስለ ነበር፣ አንዳች እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ሲነጋም ኢየሱስ ወደ ምድረ በዳም ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ እርሱ ወዳለበትም ቦታ መጡ፤ ከእነርሱ ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ሞከሩ። እርሱ ግን፣ “ወደ ሌሎቹም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል፤ የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነውና” አላቸው። በይሁዳም በምኵራቦች መስበኩን ቀጠለ።

ሉቃስ 4:33-44 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በምኵራብም የርኵስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኾ፦ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ። ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። ሁሉንም መደነቅ ያዛቸው፥ እርስ በርሳቸውም፦ ይህ ቃል ምንድር ነው? በሥልጣንና በኃይል ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛልና፥ ይወጡማል ብለው ተነጋገሩ። ዝናም በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ። በምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ንዳድ ታማ ነበር ስለ እርስዋም ለመኑት። በአጠገብዋም ቆሞ ንዳዱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ያንጊዜውንም ተነሥታ አገለገለቻቸው። ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። አጋንንትም ደግሞ፦ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ገሠጻቸውም ክርስቶስም እንደ ሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። በጸባም ጊዜ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፥ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ወደዱ። እርሱ ግን፦ ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል አላቸው። በገሊላም ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።

ሉቃስ 4:33-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እዚያም በምኲራብ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ነበር፤ እርሱ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።” ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ፥ “ዝም ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ሲል ገሠጸው፤ ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን በሕዝቡ ፊት ጣለውና ምንም ሳይጐዳው ወጣ። ሁሉም በመደነቅ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ምን ዐይነት ቃል ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዛል፤ እነርሱም ታዘው ይወጣሉ፤” ተባባሉ። የኢየሱስም ዝና በዚያ አገር ዙሪያ ሁሉ ተሰማ። ኢየሱስ ከምኲራብ ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ሄደ፤ እዚያም የስምዖን ዐማት በጣም አተኲሶአት ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለዚህ እንዲያድናት ኢየሱስን ለመኑት። ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀርቦ አጠገብዋ ቆመና ትኲሳቱ እንዲለቃት አዘዘ፤ ትኲሳቱም ለቀቃት፤ ወዲያውኑም ተነሥታ ታስተናግዳቸው ጀመር። ፀሐይ ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕመምተኞች ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን በመጫን ፈወሳቸው። አጋንንትም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ በመጮኽ ብዙ ሰዎችን እየለቀቁ ይወጡ ነበር፤ እርሱ መሲሕ መሆኑንም ዐውቀው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ስለ እርሱ ምንም እንዳይናገሩ በመገሠጽ ይከለክላቸው ነበር። በነጋም ጊዜ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሰው ወደሌለበት ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ ሰዎቹም ይፈልጉት ነበር፤ ባገኙትም ጊዜ “ተለይተኸን አትሂድብን” ብለው ለመኑት። እርሱ ግን “እኔ የተላክሁት ለዚህ ስለ ሆነ ወደ ሌሎችም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው። ስለዚህ በይሁዳም ምኲራቦች ሁሉ እየተዘዋወረ ይሰብክ ነበር።

ሉቃስ 4:33-44 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ በታላቅ ድምፅም ጮኾ፦ “ተው፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደሆንህ አውቄሃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ዝም በል፤ ከእርሱም ውጣ፤” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ምንም ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። ሁሉም ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፦ “ይህ ቃል ምንድነው? በሥልጣንና በኃይል ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፥ እነርሱም ይወጣሉ፤” እያሉ ይነጋገረሩ ነበር። ስለ እርሱም የተነገረው በዙሪያው ባለው አገር፥ በሁሉ ስፍራ ተሰራጭቶ ነበር። ከምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ትኩሳት ታማ ነበር፤ ስለ እርሷም ለመኑት። በአጠገብዋም ቆሞ ትኩሳቱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው። ፀሐይም ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕሙማን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። አጋንንትም ደግሞ፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” ብለው እየጮኹ ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፥ ምክንያቱም ክርስቶስ እንደሆነ አውቀውት ነበርና። ሲነጋም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፤ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ይጥሩ ነበር። እርሱ ግን፦ “የተላክሁት በዚሀ ምክንያት ነውና ለሌሎቹ ከተማዎችም የእግዚአብሔርን መንግሥት መልካም ዜና ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው። እርሱም በይሁዳ በሚገኙት ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።