ሉቃስ 4:1-22

ሉቃስ 4:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መን​ፈስ ቅዱ​ስን ተመ​ልቶ ከዮ​ር​ዳ​ኖስ ተመ​ለሰ፤ መን​ፈ​ስም ወደ ምድረ በዳ ወሰ​ደው። አርባ መዓ​ል​ትና አርባ ሌሊት ከዲ​ያ​ብ​ሎስ ተፈ​ተነ፥ በእ​ነ​ዚ​ያም ቀኖች ምንም አል​በ​ላም፤ እነ​ዚ​ያም ቀኖች ከተ​ፈ​ጸሙ በኋላ ተራበ። ዲያ​ብ​ሎ​ስም፥ “አንተ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ከሆ​ን​ህስ ይህ ድን​ጋይ እን​ጀራ ይሁን በል” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ሰው የሚ​ኖ​ረው ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አፍ በሚ​ወ​ጣው ቃል ነው እንጂ በእ​ን​ጀራ ብቻ አይ​ደ​ለም የሚል ተጽ​ፎ​አል” አለው። ዲያ​ብ​ሎ​ስም ወደ ረዥም ተራራ አወ​ጣው፤ የዓ​ለ​ምን መን​ግ​ሥ​ታ​ትም ሁሉ በቅ​ፅ​በት አሳ​የው። ዲያ​ብ​ሎ​ስም እን​ዲህ አለው፥ “ይህን ሁሉ ግዛት፥ ይህ​ንም ክብር ለአ​ንተ እሰ​ጥ​ሃ​ለሁ፤ ለእኔ ተሰ​ጥ​ቶ​አ​ልና፤ ለወ​ደ​ድ​ሁ​ትም እሰ​ጠ​ዋ​ለ​ሁና። ስለ​ዚህ አንተ በፊቴ ብት​ሰ​ግ​ድ​ልኝ ይህ ሁሉ ለአ​ንተ ይሁ​ን​ልህ።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ሰይ​ጣን ከኋ​ላዬ ሂድ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለአ​ም​ላ​ክህ ልት​ሰ​ግድ፥ እር​ሱ​ንም ብቻ ልታ​መ​ልክ ተጽ​ፎ​አል” አለው። ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ወስዶ በቤተ መቅ​ደሱ የማ​ዕ​ዘን ጫፍ ላይ አቆ​መው፤ እን​ዲ​ህም አለው፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ከሆ​ን​ህስ አንተ ራስህ ወደ ታች መር ብለህ ውረድ። በመ​ን​ገ​ድህ ይጠ​ብ​ቁህ ዘንድ መላ​እ​ክ​ትን ስለ አንተ ያዝ​ዛ​ቸ​ዋል፤ እግ​ር​ህም በድ​ን​ጋይ እን​ዳ​ት​ሰ​ነ​ካ​ከል በእ​ጃ​ቸው ያነ​ሡ​ሃል” ተብሎ ተጽ​ፎ​አ​ልና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ፈጣ​ሪህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አት​ፈ​ታ​ተ​ነው” ተብ​ሎ​አል አለው። ዲያ​ብ​ሎ​ስም በዚህ ሁሉ እር​ሱን መፈ​ታ​ተ​ኑን ከፈ​ጸመ በኋላ እስከ ጊዜው ከእ​ርሱ ተለየ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም በመ​ን​ፈስ ቅዱስ ኀይል ተመ​ልሶ ወደ ገሊላ ሄደ፤ ዝና​ውም በሀ​ገሩ ሁሉ ተሰማ። በየ​ም​ኵ​ራ​ባ​ቸ​ውም ሁሉ ያስ​ተ​ም​ራ​ቸው ነበር፤ ትም​ህ​ር​ቱ​ንም ያደ​ንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመ​ሰ​ግ​ኑት ነበር። ወደ አደ​ገ​በት ወደ ናዝ​ሬ​ትም ሄደ፤ በሰ​ን​በት ቀንም እን​ዳ​ስ​ለ​መደ ወደ ምኵ​ራብ ገባ፤ ሊያ​ነ​ብም ተነሣ። የነ​ቢ​ዩን የኢ​ሳ​ይ​ያ​ስ​ንም መጽ​ሐፍ ሰጡት፤ መጽ​ሐ​ፉ​ንም በገ​ለጠ ጊዜ እን​ዲህ የሚል የተ​ጻ​ፈ​በ​ትን ስፍራ አገኘ። “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈስ በላዬ ነው፤ ስለ​ዚህ ቀብቶ ለድ​ሆች የም​ሥ​ራ​ችን እነ​ግ​ራ​ቸው ዘንድ፥ ለተ​ማ​ረ​ኩ​ትም ነጻ​ነ​ትን እሰ​ብ​ክ​ላ​ቸው ዘንድ፥ ያዘ​ኑ​ት​ንም ደስ አሰ​ኛ​ቸው ዘንድ፥ ዕው​ሮ​ችም ያዩ ዘንድ፥ የተ​ገ​ፉ​ት​ንም አድ​ና​ቸው ዘንድ፥ የታ​ሰ​ሩ​ት​ንም እፈ​ታ​ቸው ዘንድ፥ የቈ​ሰ​ሉ​ት​ንም አድ​ና​ቸው ዘንድ፥ የተ​መ​ረ​ጠ​ች​ው​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ዓመት እሰ​ብክ ዘንድ ላከኝ።” መጽ​ሐ​ፉ​ንም አጥፎ ለተ​ላ​ላ​ኪው ሰጠ​ውና ተቀ​መጠ፤ በም​ኲ​ራ​ብም የነ​በ​ሩት ሁሉ ዐይ​ና​ቸ​ውን አት​ኲ​ረው ተመ​ለ​ከ​ቱት። እር​ሱም፥ “የዚህ የመ​ጽ​ሐፍ ነገር ዛሬ በጆ​ሮ​አ​ችሁ ደረሰ፤ ተፈ​ጸ​መም” ይላ​ቸው ጀመር። ሁሉም የን​ግ​ግ​ሩን መከ​ና​ወን መሰ​ከ​ሩ​ለት፤ የአ​ን​ደ​በ​ቱ​ንም ቅል​ጥ​ፍና እያ​ደ​ነቁ፥ “ይህ የዮ​ሴፍ ልጅ አይ​ደ​ለ​ምን?” ይሉ ነበር።

ሉቃስ 4:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ፣ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፤ በዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀናት ምንም ሳይበላ ከቈየ በኋላ በመጨረሻ ተራበ። ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዘው” አለው። ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ዲያብሎስ ወደ አንድ ከፍታ ቦታ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው፤ እንዲህም አለው፤ “የእነዚህ መንግሥታት ሥልጣንና ክብር ሁሉ ለእኔ ተሰጥቷል፤ እኔም ለምወድደው ስለምሰጥ፣ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።” ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘ይጠብቁህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል፤ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይጋጭ፣ በእጆቻቸው ያነሡሃል።’ ” ኢየሱስም፣ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሏል” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስ ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ። ኢየሱስም በመንፈስ ኀይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር ነበር፤ ሰውም ሁሉ ያመሰግነው ነበር። ከዚያም ወዳደገበት ከተማ ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብብም ተነሥቶ ቆመ። የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም መጽሐፍ በተረተረው ጊዜ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ክፍል አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ከዚያም መጽሐፉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብ የነበሩትም ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፣ “ይህ በጆሯችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ይላቸው ጀመር። ሁሉም ስለ እርሱ በበጎ ይናገሩ ነበር፤ ደግሞም ከአንደበቱ በሚወጣ የጸጋ ቃል እየተገረሙ፣ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።

ሉቃስ 4:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። ዲያብሎስም፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ፦ እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። ኢየሱስም፦ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው። ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቁሞ፦ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፥ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው። ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ፦ ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር።

ሉቃስ 4:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተመለሰ፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ በረሓ ሄደ። እዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀኖች ምንም ስላልበላ በመጨረሻ ተራበ። ዲያብሎስም ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ” አለው። ኢየሱስም፦ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ አንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። “ይህን ሁሉ ሥልጣንና ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህ ሁሉ ለእኔ የተሰጠኝ ስለ ሆነ ለፈለግሁት መስጠት እችላለሁ፤ ስለዚህ አንተ ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ለጌታ ለአምላክህ ብቻ ስገድ! እርሱንም ብቻ አምልክ! ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት። ከዚያም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ በቤተ መቅደሱም ጣራ ጫፍ ላይ እንዲቆም አድርጎ፥ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ እስቲ ከዚህ ወደታች ዘለህ ውረድ፤ ‘አንተን እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዛል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል፥ በእጃቸው ደግፈው ይይዙሃል፥’ ተብሎ ተጽፎአልና፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው፥’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት። ዲያብሎስ ኢየሱስን መፈተኑን ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ትቶት ሄደ። ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተሞልቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አካባቢዎች ሁሉ ተሰማ። በምኲራቦቻቸውም ያስተምር ነበር፤ ሁሉም በትምህርቱ አመሰገኑት። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ አደገበት አገር ወደ ናዝሬት ሄደ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኲራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ፤ የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤ ለታሰሩት መፈታትን፥ ለዕውሮች ማየትን እንዳውጅና የተጨቈኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤ እንዲሁም ጌታ ሕዝቡን የሚያድንበትን የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል።” ኢየሱስ መጽሐፉን አጥፎ ለአስተናባሪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራቡ የነበሩትም ሁሉ ትኲር ብለው ወደ እርሱ ይመለከቱ ጀመር፤ እርሱም “እነሆ! ይህ አሁን ሲነበብ የሰማችሁት የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው። ስለ እርሱ ሁሉም መልካም ይናገሩ ነበር፤ በሚናገረውም ጸጋን የተመላ ቃል ተደንቀው “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” አሉ።

ሉቃስ 4:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም በመንፈስ ተመራ። ለአርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ። በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ ቀኖቹም በተፈጸሙ ጊዜ ተራበ። ዲያብሎስም፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ከፍ ወዳለው ስፍራ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ “ለአንተ ይህን ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውንም እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥተቶአልና ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” አለው። ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቆመው፥ እንዲህም አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር፤ እነሆ፥ ‘አንተን ለመጠበቅ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል አንተን በእጃቸው ያነሡሃል፤’ ተብሎ ተጽፎአልና።” ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው፤’ ተብሏል፤” አለው። ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ከእርሱ ተለየ። ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተወራ። እንዲሁም በሁሉም እየተመሰገነ በምኵራባቸው ያስተምር ነበር። ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደተለመደው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩም የኢሳይያስ ጥቅል ብራና ተሰጠው፤ ጥቅሉንም በዘረጋው ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች መልካም ዜናን እንዳበሥር ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዐይነ ስውሮችም ማየትን እንዳውጅ፥ የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ጥቅል ብራናውንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ከሰጠ በኋላ ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ “ዛሬ ይህ በጆሮዎቻችሁ የሰማችሁት ጽሑፍ ተፈጸመ፤” ይላቸው ጀመር። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር፤ ከአፉም ከሚወጡት ቃላት ጸጋ የተነሣ እየተደነቁ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።