ሉቃስ 24:13-49
ሉቃስ 24:13-49 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያም ቀን ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደምትርቀው ኤማሁስ ወደምትባለው መንደር ሄዱ። እርስ በርሳቸውም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ ይነጋገሩ ነበር። እነርሱም ይህን ሲነጋገሩና ሲመራመሩ ጌታችን ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ አብሮአቸውም ሄደ። እንዳያውቁትም ዐይናቸው ተይዞ ነበር። ጌታችንም፥ “በትካዜ እየሄዳችሁ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። ከእነርሱም ቀለዮጳ የሚባለው አንዱ መልሶ፥ “አንተ ብቻ ለኢየሩሳሌም እንግዳ ነህን? በእነዚህ ቀኖችስ በውስጥዋ የተደረገውን አታውቅምን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህ ምንድነው?” አላቸው፤ እነርሱም እንዲህ አሉት፥ “በእግዚአብሔር ፊትና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በቃሉና በሥራው ብርቱ ነቢይና እውነተኛ ሰው ስለነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፥ የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን አሳልፈው እንደ ሰጡት፥ ሞትም እንደ ፈረዱበትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ እናደርግ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ይህ ነገር ከሆነ ዛሬ ሦስተኛ ቀን ነው። ደግሞም ሴቶች ከእኛ ዘንድ ወደ መቃብር ገስግሠው ሄደው ነበርና አስደንቀው ነገሩን። ሥጋውንም በአላገኙ ጊዜ ተመልሰው፦ ተነሥቶአል ያሉአቸውን የመላእክትን መልክ እንደ አዩ ነገሩን። ከእኛም ዘንድ ወደ መቃብር ሄደው እንዲሁ ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ ያገኙት አሉ፤ እርሱን ግን አላዩትም።” ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰነፎች፥ ነቢያትም የተናገሩትን ነገር ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ፥ ክርስቶስ እንዲህ ይሞት ዘንድ ወደ ክብሩም ይመለስ ዘንድ ያለው አይደለምን?” እርሱም ከሙሴና ከነቢያት፥ ከመጻሕፍትም ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን ይተረጕምላቸው ጀመር። ሊሄዱባት ወደ ነበረችው መንደርም ተቃረቡ፤ እርሱ ግን ይርቃቸው ጀመር። እነርሱም፥ “መሽቶአልና፥ ፀሐይም ተዘቅዝቆአልና፥ ከእኛ ጋር እደር” ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። ከዚህም በኋላ አብሮአቸው ለማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። ዐይናቸውም ተገለጠና ዐወቁት፤ ወዲያውኑም ከእነርሱ ተሰወረ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ አሉ፥ “በመንገድ ሲነግረን፥ መጻሕፍትንም ሲተረጕምልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርትና አብረዋቸው የነበሩትንም ተሰብስበው አገኙአቸው፤ እንዲህ እያሉ፥ “ጌታችን በእውነት ተነሥቶአል፤ ለስምዖንም ታይቶታል።” እነርሱም በመንገድ የሆነውንና እንጀራውን ሲቈርስ ጌታችንን እንዴት እንዳወቁት ነገሩአቸው። ይህንም ሲነጋገሩ ጌታችን ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አትፍሩ፤ እኔ ነኝ” አላቸው። እነርሱ ግን ፈሩ፤ ደነገጡም፤ ምትሐትንም የሚያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ምን ያስደነግጣችኋል? በልባችሁስ እንዲህ ያለ ዐሳብ ለምን ይነሣሣል? እጄንና እግሬን እዩ፤ ዳስሱኝም፤ እኔ እንደ ሆንሁም ዕወቁ፤ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና።” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። ከድንጋጤ የተነሣም ገና ሳያምኑ ደስ ብሎአቸውም ሲያደንቁ ሳሉ፥ “በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፤ ከማር ወለላም ጥቂት ሰጡት። ተቀብሎም በፊታቸው በላ፤ የተረፈውንም አንሥቶ ሰጣቸው። እርሱም፥ “በሙሴ ኦሪት፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ እንዳለው፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የነገርኋችሁ ነገሬ ይህ ነው” አላቸው። ከዚህም በኋላ መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው፥ “ክርስቶስ እንዲሞት በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንዲነሣ፥ ንስሓና የኀጢኣት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንዲሰበክ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ነገር ምስክሮች ናችሁ። እነሆ፥ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ።”
ሉቃስ 24:13-49 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር። እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት። እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ዐልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየተገባደደ ስለሆነ ከእኛ ጋር ዕደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ። አብሯቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ፣ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በርግጥ ተነሥቷል! ለስምዖንም ታይቷል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቍራሽ ሰጡት፤ እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
ሉቃስ 24:13-49 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው። ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም። እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው። እነርሱ፦ ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እርስ በርሳቸውም፦ በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ። በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም፦ ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው። ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም፦ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፦ በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ። እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።
ሉቃስ 24:13-49 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያኑ ቀን ከኢየሱስ ተከታዮች ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያኽል ርቃ ወደምትገኝ ኤማሁስ ተብላ ወደምትጠራ መንደር ይጓዙ ነበር። እነርሱም ይህን የሆነውን ነገር ሁሉ አንሥተው እርስ በእርሳቸው ይወያዩ ነበር። ይህንንም በሚያወሩበትና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሮአቸው ይጓዝ ጀመር። ነገር ግን በዐይናቸው እያዩት ማን እንደ ሆነ ማወቅ አልቻሉም። እርሱም “በጒዞ ላይ ሳላችሁ የምትነጋገሩበት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እያዘኑ ቀጥ ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው፥ “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “ምንድን ነው እርሱ?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለ ተፈጸመው ነገር ነዋ! እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች ሁሉ ፊት በቃልና በሥራ ብርቱ የሆነ ነቢይ ነበር። የካህናት አለቆችና መሪዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ እንዲሁም ሰቀሉት። እኛ ግን ‘እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው’ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ እነሆ፥ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። እንዲያውም ከእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ ሴቶች አስገርመውናል፤ እነርሱ ዛሬ በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ነገር ግን የእርሱን አስከሬን አላገኙም፤ ‘ሕያው ሆኖአል!’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን እያሉም ተመልሰው መጡ። ከእኛም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙ፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉና ነቢያት የተናገሩትንም ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! መሲሕ ይህን ሁሉ መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት መጻሕፍት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ አስረዳቸው። እነርሱ ወደሚሄዱበት መንደር በቀረቡ ጊዜ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን “ቀኑ መሽቶአል፤ ፀሐይም መጥለቅዋ ነው፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር እዚህ ዕደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋር ሊያድር ወደ ቤት ገባ። ከእነርሱም ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ እንጀራ አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ቈርሶ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተና ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ ግን ወዲያው ከዐይናቸው ተሰወረ። እነርሱም እርስ በርሳቸው “በመንገድ ሳለን ሲነግረንና ቅዱሳት መጻሕፍትንም እየጠቀሰ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠል አልነበረምን?” ተባባሉ። እነርሱም በዚያችው ሰዓት ተነሡና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ፤ በዚያም ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርት አብረዋቸው ካሉት ጋር በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል!” ይሉ ነበር። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው በመንገድ ላይ የሆነውን ነገርና ጌታ ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁትም ተረኩላቸው። እነርሱም ይህን ሲናገሩ ሳሉ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱ ግን መንፈስ የሚያዩ መስሎአቸው ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትደነግጣላችሁ፤ ስለምንስ በልባችሁ ትጠራጠራላችሁ? እጆቼንና እግሮቼን አይታችሁ እኔ ራሴ መሆኔን ዕወቁ፤ ዳሳችሁም እዩኝ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም።” ይህንንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው፤ እነርሱም ከደስታና ከአድናቆት ብዛት የተነሣ ገና አላመኑም ነበር። ኢየሱስም “አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት። እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። ኢየሱስም፥ “ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ የነገርኳችሁ ቃል ይህ ነው” አላቸው። ከዚህ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተዋል እንዲችሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው፤ “መሲሕ መከራ እንደሚቀበልና በሦስተኛው ቀን ከሞት እንደሚነሣ አስቀድሞ ተጽፎአል፤ እንዲሁም በስሙ የንስሓና የኃጢአት ይቅርታ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በየአገሩ ለሕዝብ ሁሉ እንደሚሰበክ ተነግሮአል። እናንተም የዚህ ሁሉ ነገር ምስክሮች ናችሁ፤ እነሆ! እኔ አባቴ የሰጣችሁን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተም ከላይ ኀይል እንደ ልብስ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
ሉቃስ 24:13-49 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም “አብራችሁ እየሄዳችሁ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?” አላቸው። እነርሱም አዝነው ቀጥ ብለው ቆሙ። ቀለዮጳ የሚባለውም አንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም የተከሠተውን ነገር የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” እርሱም “ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ነው፤ የካህናት አለቆቻችንና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን የሚታደገው እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም ይህ ነገር ከሆነ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። አስከሬኑንም ባጡ ጊዜ ‘ሕያው ነው’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛ ጋር ከነበሩት አንዳንዶች ወደ መቃብር ሄደው ሴቶቹ እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉ፤ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን አብራራላቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፤ እርሱም አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን “እኛ ጋር እደር፤ እየመሸ ነው፥ ቀኑም እያለቀ ነውና፤” ሲሉ አጥብቀው ለመኑት፤ እርሱም እነርሱ ጋር ሊያድር ገባ። ከእነርሱም ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፤ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዐይናቸውም ተከፈተና አወቁት፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እርስ በርሳቸውም “በመንገድ ሳለን ሲያናግረንና መጻሕፍትንም ሲያስረዳን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትንም በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ በእርግጥ ተነሥቷል፥ ለስምዖንም ታይቷል” ይሉ ነበር። እነርሱም በመንገድ የሆነውን፥ እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህንንም ሲነጋገሩ ሳለ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው “ስለምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ያድራል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ ዳስሱኝና እዩ፥ መንፈስ በእኔ እንደምታዩት፥ ሥጋና አጥንት የለውምና፤” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ ብዛት ገና ሳያምኑ ገና በመገረም ላይ ሳሉ “በዚህ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ። ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው “እንዲህ ተጽፏል፥ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንደሚሰበክ፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በዚህች ከተማ ቆዩ።”