ሉቃስ 24:1-7
ሉቃስ 24:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሳምንቱም በመጀመሪያዪቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ። ያቺንም ድንጋይ ከመቃብሩ ላይ ተንከባልላ አገኙአት። ገብተውም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። ስለዚህም ነገር የሚሉትን አጥተው ሲያደንቁ ሁለት ሰዎች ከፊታቸው ቆመው ታዩአቸው፤ ልብሳቸውም ያብረቀርቅ ነበር። ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀረቀሩ። እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፥ “ሕያዉን ከሙታን ጋር ለምን ትሹታላችሁ? በዚህ የለም፤ ተነሥቶአል። በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንዲህ ሲል የተናገረውን ዐስቡ፦ የሰው ልጅ በኀጢኣተኞች ሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይሰቅሉታል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” 10፥33-34፤ ሉቃ. 9፥22፤ 18፥31-33።
ሉቃስ 24:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው እጅግ ማለዳ ሳለ ወደ መቃብሩ ሄዱ። ድንጋዩም ከመቃብሩ ደጃፍ ተንከባልሎ አገኙት፤ ወደ ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። በሁኔታው ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ እነሆ፤ እጅግ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ። ሴቶቹም ከመፍራታቸው የተነሣ በምድር ተደፍተው ሳሉ፣ ሰዎቹ እንዲህ አሏቸው፤ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቷል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና።”
ሉቃስ 24:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው፦ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ።
ሉቃስ 24:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) ጠዋት በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት። ወደ ውስጥ በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። ስለዚህም ነገር በመገረም ላይ ሳሉ እነሆ፥ የሚያንጸባርቅ ብሩህ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች መጥተው በአጠገባቸው ቆሙ። ሴቶቹም እጅግ ፈርተው ወደ መሬት አቀርቅረው ሳሉ ሰዎቹ፦ “ስለምን ሕያውን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? አሉአቸው። እርሱ እዚህ የለም፤ ተነሥቶአል፤ በገሊላ በነበረበት ጊዜ የነገራችሁን አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች ተላልፎ መሰጠት፥ መሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ከሞት መነሣት ይገባዋል’ ብሎአችሁ ነበር።”
ሉቃስ 24:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልደው፥ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት፤ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲገረሙ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው “ሕያዉን ለምን በሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እርሱ እዚህ የለም፤ ይልቁንም ተነሥቶአል። ገና በገሊላ እያለ የነገራችሁን አስታውሱ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው።”