ሉቃስ 23:27-31
ሉቃስ 23:27-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና። ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን’ ይሉአቸዋል። በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?”
ሉቃስ 23:27-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያን ጊዜም፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሰውሩን!” ’ ይላሉ። እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?”
ሉቃስ 23:27-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን፦ በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም፦ ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?
ሉቃስ 23:27-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?”
ሉቃስ 23:27-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?”