ሉቃስ 23:26-34
ሉቃስ 23:26-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በወሰዱትም ጊዜ የቀሬና ሰው ስምዖንን ከዱር ሲመለስ ያዙት፤ ከጌታችን ከኢየሱስም በስተኋላ መስቀሉን አሸከሙት። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና። ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን’ ይሉአቸዋል። በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?” ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችንም ከእርሱ ጋር ሊሰቅሉ ወሰዱ። ቀራንዮ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜም፥ በዚያ ሰቀሉት፤ እነዚያንም ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን ኣያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጣሉና ተካፈሉ።
ሉቃስ 23:26-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት። ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያን ጊዜም፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሰውሩን!” ’ ይላሉ። እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?” ከእርሱ ጋር እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት።
ሉቃስ 23:26-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት። ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን፦ በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም፦ ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን? ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋር ይገድሉ ዘንድ ወሰዱ። ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት።
ሉቃስ 23:26-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ኢየሱስን ወሰዱት፤ ይዘውት ሲሄዱ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ እርሱን ይዘው የኢየሱስን መስቀል አሸከሙትና ኢየሱስን እንዲከተል አደረጉት። ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” እንዲሁም ሁለት ወንጀለኞችን ከኢየሱስ ጋር ሊገድሉአቸው ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት፤ እንዲሁም ሁለቱን ወንጀለኞች በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉአቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” አለ። ወታደሮቹም ዕጣ ተጣጥለው የኢየሱስን ልብስ ተከፋፈሉ።
ሉቃስ 23:26-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው ያዙትና መስቀሉን ጭነውበት ከኢየሱስ በኋላ እንዲሄድ አደረጉት። ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?” ሌሎችም ሁለት ክፉ አድራጊዎችንም ከእርሱ ጋር ለመግደል ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ እርሱን፥ ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው በኩል ሰቀሉ። ኢየሱስም “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤” አለ። ልብሱንም ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉት።