ሉቃስ 19:28-48
ሉቃስ 19:28-48 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ተናግሮ ወደ ፊት ሄደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ወጣ። ደብረ ዘይት ወደሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ። እንዲህም አላቸው፥ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ገብታችሁም ሰው ያልተቀመጠበት የታሰረ ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ። ለምን ትፈቱታላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ።” የተላኩትም ሄደው እንደ አላቸው አገኙ። ውርንጫውንም ሲፈቱ ባለቤቶቹ “ውርንጫውን ለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ጌታው ይሻዋል” አሉ። ይዘውም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱት፤ በውርንጫው ላይም ልብሳቸውን ጭነው ጌታችን ኢየሱስን በዚያ ላይ አስቀመጡት። ሲሄዱም በመንገድ ልብሳቸውን አነጠፉ። ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት መውረጃም በደረሱ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ስለ አዩት ኀይል ሁሉ ደስ ይላቸውና እግዚአብሔርን በታላቅ ቃል ያመሰግኑት ዘንድ ጀመሩ። እንዲህ እያሉ፥ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ የእስራኤል ንጉሥ ቡሩክ ነው፤ ሰላም በምድር፥ በአርያምም ክብር ይሁን።” ከፈሪሳውያንም በሕዝቡ መካከል፥ “መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ያሉት ነበሩ። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እነዚህ ዝም ቢሉ እኒህ ድንጋዮች ይጮሀሉ።” በደረሰ ጊዜም ከተማዪቱን አይቶ አለቀሰላት። እንዲህም አላት፥ “አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበረ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ። ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል። አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጥሉአቸዋል፤ ድንጋይንም በደንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና።” ወደ ቤተ መቅደስም ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የለዋጮችንም መደርደሪያ፥ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ። “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል የሚል ጽሑፍ አለ፤ እናንተ ግን የሌቦችና የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። ዘወትርም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝብ ታላላቆችም ሊገድሉት ይሹ ነበር። ነገር ግን የሚያደርጉትን አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ትምህርቱን በመስማት ይመሰጡ ነበርና።
ሉቃስ 19:28-48 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሟቸው ይሄድ ነበር። ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።” የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው። እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ። ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሶቻቸውን በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሶቻቸውን ያነጥፉ ነበር። በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል ወደሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤ “በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!” “በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት። እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው። ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ፤ “ሰላምሽ የሚሆነውን ምነው አንቺ ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሯል፤ ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከብበው አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣልና፤ አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላወቅሽምና።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ ሻጮችን ከዚያ ያስወጣ ጀመር፤ ደግሞም “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በየቀኑም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከርሱ ጋራ ተቈራኝተው ትምህርቱን ይከታተሉ ስለ ነበር፣ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው።
ሉቃስ 19:28-48 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት። ማንም፦ ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ፦ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው። የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ። እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ፦ ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም እነርሱም፦ ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ። ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት። ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር። ወደ ደብረ ዘይት ቍልቍለትም አሁን በቀረበ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁላቸው ደስ እያላቸው ተአምራትን ሁሉ ስላዩ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ጀምረው፦ በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ። ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ፦ መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። መልሶም፦ እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው። ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ፦ ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና። ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፤ እርሱም፦ ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው። ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥ የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።
ሉቃስ 19:28-48 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ጒዞውን ወደ ኢየሩሳሌም በመቀጠል፥ ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወደሚገኙት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወደምትገኘው መንደር ሂዱ፤ እዚያም በደረሳችሁ ጊዜ ገና ማንም ሰው ያልተቀመጠበትን የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወዲህ አምጡት። ማንም ሰው ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ ‘ጌታ ስለሚያስፈልገው ነው’ ብላችሁ መልሱለት።” የተላኩትም ሄደው ሁሉም ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት። ውርንጫውን በሚፈቱበት ጊዜ ባለቤቶቹ፦ “ስለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ለጌታ ስለሚያስፈልገው ነው” አሉ። ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ ልብሳቸውንም በውርንጫው ጀርባ ላይ አንጥፈው ኢየሱስ እንዲቀመጥበት አደረጉ። ኢየሱስ ሲሄድ ሳለ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገዱ ላይ ያነጥፉለት ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ሊደርስ በተቃረበ ጊዜ የደብረ ዘይትን ተራራ ቊልቊል በመውረድ ላይ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ስላዩአቸው ተአምራት በደስታ ተሞልተው ስለ ነበር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመሩ። እንዲህ ይሉም ነበር፤ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው! ሰላም በሰማይ፥ ክብርም ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን!” በሕዝቡ መካከል የነበሩት አንዳንድ ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን “መምህር ሆይ! ደቀ መዛሙርትህን ዝም አሰኛቸው!” አሉት። ኢየሱስም “እነርሱ እንኳ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ እላችኋለሁ” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ቀርቦ፥ ከተማይቱን በተመለከተ ጊዜ፥ አለቀሰላት። እንዲህም አለ፤ “አንቺ ለሰላምሽ የሚያስፈልገውን ነገር ምነው ዛሬ ዐውቀሽ ቢሆን ኖሮ! አሁን ግን ይህ ነገር ከዐይንሽ ተሰውሮብሻል፤ ጠላቶችሽ በዙሪያሽ ዐጥር ዐጥረውና ከበው፥ በዚህም በዚያም አንቺን የሚያስጨንቁበት ቀን ይመጣል። አንቺንና በውስጥሽ ያሉትንም ልጆችሽን በመሬት ላይ ጥለው ያወድማሉ፤ ሳይፈርስ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ በቦታው አይተዉልሽም፤ ይህም የሚሆነው፥ እግዚአብሔር አንቺን ሊያድን የመጣበትን ጊዜ ባለማወቅሽ ነው።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፥ በዚያ የሚገበያዩትን ሰዎች ማባረር ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።” ኢየሱስ በየቀኑ በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን፥ ሌሎችም የሕዝብ መሪዎች ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመስማት በመፈለግ ልባቸው ተማርኮ ስለ ነበረ ሊገድሉት የፈለጉት ወገኖች ምንም ማድረግ አልቻሉም።
ሉቃስ 19:28-48 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ደብረዘይት በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበም ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ እርሷም ገብታችሁ ገና ማንም ሰው ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡት። ማንም ‘ስለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤’ በሉ”። የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው ሆኖ አገኙት። እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ “ውርንጫውን ስለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ለጌታ ያስፈልገዋል፥” አሉ። ወደ ኢየሱስም አመጡት፤ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ወርውረው ኢየሱስን አስቀመጡት። ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር። ወደ ደብረዘይት ቁልቁለትም ወዲያው በቀረበ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ በሙሉ ስላዩአቸው ተአምራት ደስ እያላቸው በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመሩ፤ እንዲህም አሉ፦ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር፥” አሉ። ከሕዝቡም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ! ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው፤” አሉት። ሲመልስም “እነዚህ እንኳ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ፤እላችኋለሁ” አላቸው። ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ እንዲህ እያለ አለቀሰላት፤ “አንቺስ ለሰላምሽ የሚሆነውን ምነው በዚህ ቀን ባወቅሽ ኖሮ! ነገር ግን አሁን ከዐይንሽ ተሰውሮአል። ጠላቶችሽም በዙርያሽ ቅጥር የሚሠሩበት፥ አንቺን የሚከቡበትና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁብት ቀኖች ይመጣሉ። አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን በምድር ላይ ይጨፈልቃሉ፤ በአንቺ ውስጥም በድንጋይ ላይ የሚኖር ድንጋይ አያስቀሩም፤ የተጐብኘሽበትን ዘመን አላወቅሽምና።” ወደ መቅደስም ገብቶ የሚገበያዩትን ማስወጣት ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው፦ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት፤” አላቸው። በየዕለቱም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ በታላቅ ትኩረት ይሰሙት ነበርና።