ሉቃስ 19:28-36
ሉቃስ 19:28-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ተናግሮ ወደ ፊት ሄደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ወጣ። ደብረ ዘይት ወደሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ። እንዲህም አላቸው፥ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ገብታችሁም ሰው ያልተቀመጠበት የታሰረ ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ። ለምን ትፈቱታላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ።” የተላኩትም ሄደው እንደ አላቸው አገኙ። ውርንጫውንም ሲፈቱ ባለቤቶቹ “ውርንጫውን ለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ጌታው ይሻዋል” አሉ። ይዘውም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱት፤ በውርንጫው ላይም ልብሳቸውን ጭነው ጌታችን ኢየሱስን በዚያ ላይ አስቀመጡት። ሲሄዱም በመንገድ ልብሳቸውን አነጠፉ።
ሉቃስ 19:28-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሟቸው ይሄድ ነበር። ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።” የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው። እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ። ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሳቸውን ያነጥፉ ነበር።
ሉቃስ 19:28-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት። ማንም፦ ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ፦ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው። የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ። እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ፦ ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም እነርሱም፦ ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ። ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት። ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር።
ሉቃስ 19:28-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ጒዞውን ወደ ኢየሩሳሌም በመቀጠል፥ ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወደሚገኙት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወደምትገኘው መንደር ሂዱ፤ እዚያም በደረሳችሁ ጊዜ ገና ማንም ሰው ያልተቀመጠበትን የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወዲህ አምጡት። ማንም ሰው ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ ‘ጌታ ስለሚያስፈልገው ነው’ ብላችሁ መልሱለት።” የተላኩትም ሄደው ሁሉም ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት። ውርንጫውን በሚፈቱበት ጊዜ ባለቤቶቹ፦ “ስለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ለጌታ ስለሚያስፈልገው ነው” አሉ። ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ ልብሳቸውንም በውርንጫው ጀርባ ላይ አንጥፈው ኢየሱስ እንዲቀመጥበት አደረጉ። ኢየሱስ ሲሄድ ሳለ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገዱ ላይ ያነጥፉለት ነበር።
ሉቃስ 19:28-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ደብረዘይት በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበም ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ እርሷም ገብታችሁ ገና ማንም ሰው ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡት። ማንም ‘ስለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤’ በሉ”። የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው ሆኖ አገኙት። እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ “ውርንጫውን ስለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። እነርሱም “ለጌታ ያስፈልገዋል፥” አሉ። ወደ ኢየሱስም አመጡት፤ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ወርውረው ኢየሱስን አስቀመጡት። ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር።