ሉቃስ 19:1-28

ሉቃስ 19:1-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ወደ ኢያ​ሪኮ ገብቶ በዚያ ያልፍ ነበር። እነሆ፥ የቀ​ራ​ጮች አለቃ ስሙ ዘኬ​ዎስ የተ​ባለ አንድ ሰው ነበር፤ እር​ሱም ባለ​ጸጋ ነበር። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስ​ንም ያየው ዘንድ፥ ማን እንደ ሆነም ያውቅ ዘንድ ይሻ ነበር፤ የሰው ብዛ​ትም ይከ​ለ​ክ​ለው ነበር፤ ቁመቱ አጭር ነበ​ርና። ወደ ፊቱም ሮጠ፤ ያየው ዘን​ድም በሾላ ላይ ወጣ፤ በዚ​ያች መን​ገድ ያልፍ ዘንድ አለ​ውና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ወደ​ዚያ በደ​ረሰ ጊዜ አሻ​ቅቦ አየ​ውና፥ “ዘኬ​ዎስ ሆይ፥ ፈጥ​ነህ ውረድ፤ ዛሬ በቤ​ትህ እውል ዘንድ አለ​ኝና” አለው። ፈጥ​ኖም ወረደ፤ ደስ እያ​ለ​ውም ወደ ቤቱ ይዞት ገባ። ሁሉም አይ​ተው “ወደ ኀጢ​ኣ​ተኛ ሰው ቤት ሊውል ገባ” ብለው አን​ጐ​ራ​ጐሩ። ዘኬ​ዎ​ስም ቆመና ጌታ​ች​ንን እን​ዲህ አለው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አሁን የገ​ን​ዘ​ቤን እኩ​ሌታ ለነ​ዳ​ያን እሰ​ጣ​ለሁ፤ የበ​ደ​ል​ሁ​ትም ቢኖር ስለ አንድ ፋንታ አራት እጥፍ እከ​ፍ​ለ​ዋ​ለሁ።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አለው፥ “ዛሬ ለዚህ ቤት ሕይ​ወት ሆነ፤ እርሱ የአ​ብ​ር​ሃም ልጅ ነውና። የሰው ልጅ የጠ​ፋ​ውን ሊፈ​ል​ግና ሊያ​ድን መጥ​ቶ​አ​ልና።” ይህ​ንም ሲሰሙ፤ ምሳሌ መስሎ ነገ​ራ​ቸው፤ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ቀርቦ ነበ​ርና፤ እነ​ር​ሱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት ወዲ​ያ​ውኑ የም​ት​ገ​ለጥ መስ​ሎ​አ​ቸው ነበ​ርና። እን​ዲ​ህም አለ፥ “አንድ የከ​በረ ሰው መን​ግ​ሥት ይዞ ሊመ​ለስ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ። ዐሥ​ሩን አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹ​ንም ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣ​ቸ​ውና፦ እን​ግ​ዲህ እስ​ክ​መ​ለስ ድረስ ነግዱ አላ​ቸው። የሀ​ገሩ ሰዎች ግን ይጠ​ሉት ነበ​ርና፥ ይህ በእኛ ላይ ሊነ​ግሥ አን​ሻም ብለው አከ​ታ​ት​ለው መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላኩ። ከዚ​ህም በኋላ፤ መን​ግ​ሥ​ትን ይዞ በተ​መ​ለሰ ጊዜ እንደ አተ​ረፉ ያውቅ ዘንድ ምናን የሰ​ጣ​ቸ​ውን ብላ​ቴ​ኖ​ቹን እን​ዲ​ያ​መ​ጡ​አ​ቸው አዘዘ። አን​ደ​ኛ​ውም መጥቶ፦ አቤቱ፥ ምና​ንህ ዐሥር ነበር፤ እነሆ ዐሥር ምናን አት​ር​ፌ​አ​ለሁ አለው። ጌታ​ውም፦ መል​ካም፥ አንተ በጎ አገ​ል​ጋይ በጥ​ቂት የታ​መ​ንህ ስለ​ሆ​ንህ በብዙ ላይ እሾ​ም​ሃ​ለሁ፤ በዐ​ሥሩ ከተ​ሞች ላይ ተሾም አለው። ሁለ​ተ​ኛ​ውም መጥቶ፦ አቤቱ፥ ምና​ንህ አም​ስት ነበር፤ አም​ስት አት​ር​ፌ​አ​ለሁ አለው። እር​ሱ​ንም፦ አን​ተም በአ​ም​ስት ከተ​ሞች ተሾም አለው። ሦስ​ተ​ኛ​ውም መጥቶ እን​ዲህ አለው፦ አቤቱ፥ በእኔ ዘንድ የነ​በ​ረ​ቺው ምና​ንህ እነ​ኋት፤ በጨ​ርቅ ጠቅ​ልዬ አኑ​ሬ​አት ነበር። አንተ ያላ​ኖ​ር​ኸ​ውን የም​ት​ወ​ስድ፥ ያል​ዘ​ራ​ኸ​ውን የም​ታ​ጭድ፥ ያል​በ​ተ​ን​ኸ​ው​ንም የም​ት​ሰ​በ​ስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ ስለ​ማ​ው​ቅህ ፈር​ቼ​ሃ​ለ​ሁና። ጌታ​ውም እን​ዲህ አለው፦ አንተ ክፉ ሰነፍ አገ​ል​ጋይ፥ እኔ ያላ​ስ​ቀ​መ​ጥ​ሁ​ትን የም​ወ​ስድ፥ ያል​ዘ​ራ​ሁ​ትን የማ​ጭድ፥ ያል​በ​ተ​ን​ሁ​ት​ንም የም​ሰ​በ​ስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታው​ቃ​ለ​ህን? እንደ ቃልህ እፈ​ር​ድ​ብ​ሃ​ለሁ። ለምን ገን​ዘ​ቤን ወደ ለዋ​ጮች አላ​ስ​ገ​ባ​ህም? እኔም መጥቼ ከት​ርፉ ጋር በወ​ሰ​ድ​ሁት ነበር። ከዚያ የቆ​ሙ​ት​ንም፦ ይህን ምናን ከእ​ርሱ ተቀ​ብ​ላ​ችሁ ዐሥር ምናን ላለው ስጡት አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም አቤቱ፥ ዐሥር ምናን ያለው አይ​ደ​ለ​ምን? አሉት። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፦ ላለው ሁሉ ይሰ​ጡ​ታል፤ ይጨ​ም​ሩ​ለ​ታ​ልም፤ የሌ​ለ​ውን ግን ያን ያለ​ው​ንም ቢሆን ይወ​ስ​ዱ​በ​ታል። ነገር ግን እነ​ዚ​ያን ልነ​ግ​ሥ​ባ​ቸው ያል​ወ​ደ​ዱ​ትን ጠላ​ቶ​ችን ወደ​ዚህ አም​ጡና በፊቴ ውጉ​አ​ቸው።” ይህ​ንም ተና​ግሮ ወደ ፊት ሄደ፤ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ወጣ።

ሉቃስ 19:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ገብቶ በዚያ ዐልፎ ይሄድ ነበር። ስሙ ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፤ ዋና ቀረጥ ሰብሳቢና ሀብታም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ የተባለው የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱ ዐጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሊያየው አልቻለም። ኢየሱስ በዚያ መንገድ ያልፍ ስለ ነበርም፣ ሊያየው ወደ ፊት ሮጦ አንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። ኢየሱስም እዚያ ቦታ ሲደርስ፣ ቀና ብሎ፣ “ዘኬዎስ ሆይ፤ ዛሬ አንተ ቤት መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” አለው። እርሱም ፈጥኖ ወርዶ በደስታ ተቀበለው። በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉም ይህን አይተው፣ “ከኀጢአተኛ ቤት ገብቶ ሊስተናገድ ነው።” በማለት ማጕረምረም ጀመሩ። ዘኬዎስ ግን ቆመና ጌታን፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ ካለኝ ሀብት ሁሉ ግማሹን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ቀምቼ ከሆነ፣ አራት ዕጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ይህ ሰው ደግሞ የአብርሃም ልጅ ስለ ሆነ፣ ዛሬ መዳን ወደዚህ ቤት መጥቷል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።” ሕዝቡ ይህን እየሰሙ ሳሉ፣ በምሳሌ መናገሩን ቀጠለ፤ ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም በመቃረቡና ሰዎቹም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚገለጥ ስለ መሰላቸው ነው። ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “አንድ መስፍን የንጉሥነትን ማዕርግ ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ከባሮቹም መካከል ዐሥሩን ወደ ራሱ ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱበት’ አላቸው። “የአገሩ ሰዎች ግን ስለ ጠሉት፤ ‘ይህ ሰው በላያችን እንዲነግሥ አንፈልግም’ ብለው ከኋላው መልእክተኞችን ላኩበት። “ይሁን እንጂ ይህ መስፍን ንጉሥ ሆኖ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ እነዚያ ባሮችም እርሱ በሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው። “የመጀመሪያው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ የሰጠኸኝ ምናን ዐሥር ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው። “ጌታውም፣ ‘አንተ ታማኝ ባሪያ፣ መልካም አድርገሃል፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ፣ በዐሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው። “ሁለተኛውም ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ የሰጠኸኝ ምናን ዐምስት ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው። “ጌታውም፣ ‘አንተ ደግሞ በዐምስት ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው። “ሌላውም አገልጋይ ቀርቦ እንዲህ አለው፤ ‘ጌታ ሆይ፤ በጨርቅ ጠቅልዬ ያቈየሁት ምናንህ ይኸው፤ አንተ ያላስቀመጥኸውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውን የምታጭድ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ ፈራሁህ።’ “ጌታውም እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ ባሪያ! በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ፤ ያላስቀመጥሁትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትን የማጭድ፣ ጨካኝ ሰው መሆኔን ካወቅህ፣ መጥቼ ገንዘቤን ከነትርፉ እንድወስድ፣ ለምን ለሚሠሩበት ሰዎች አልሰጠህም?’ “ጌታውም እዚያ የቆሙትን፣ ‘ምናኑን ውሰዱበትና ዐሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው። “እነርሱም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ እርሱ እኮ ዐሥር ምናን አለው’ አሉት። “እርሱም እንዲህ አለ፤ ‘እላችኋለሁ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ነገር ግን እኔ በላያቸው እንዳልነግሥ የፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ዕረዷቸው።’ ” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሟቸው ይሄድ ነበር።

ሉቃስ 19:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወደ ኢያሪኮም ገብቶ ያልፍ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው፥ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፥ ባለ ጠጋም ነበረ። ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው። በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና፦ ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው፦ ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን፦ ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ኢየሱስም፦ እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ። ስለዚህም እንዲህ አላቸው፦ አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና፦ እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው። የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና፦ ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ። መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ። የፊተኛውም ደርሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው። እርሱም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው። ሁለተኛውም መጥቶ፦ ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው። ይህንም ደግሞ፦ አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው። ሌላውም መጥቶ፦ ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው። እርሱም፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው? እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው። በዚያም ቆመው የነበሩትን፦ ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው። እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት። እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል። ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው። ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር።

ሉቃስ 19:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ከተማ ገብቶ በዚያ በኩል አልፎ እየሄደ ነበር። በዚያም አንድ የቀራጮች አለቃ ዘኬዎስ የሚባል ሀብታም ሰው ነበረ። እርሱ ኢየሱስ የቱ እንደ ሆነ ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ቁመቱ አጭር በመሆኑ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሊያየው አልቻለም። ኢየሱስ በዚያ በኩል ያልፍ ስለ ነበር ዘኬዎስ እርሱን ለማየት ብሎ ከሕዝቡ ፊት ቀድሞ ሮጠና በአንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ ቀና ብሎ ተመለከተና ዘኬዎስን፥ “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በአንተ ቤት መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ከዛፉ ውረድ” አለው። ዘኬዎስም ቶሎ ብሎ ወረደና፥ በደስታ ኢየሱስን በቤቱ ተቀበለው። ይህን የተመለከቱ ሰዎች ሁሉ “ይህ ሰው ወደ ኃጢአተኛ ቤት ሊጋበዝ ገባ!” ብለው በኢየሱስ ላይ አጒረመረሙ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታ ኢየሱስን እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ ካለኝ ሀብት ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ በማታለል ከሰው ላይ የወሰድኩትም ገንዘብ ቢኖር፥ አራት እጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ።” ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “ይህ ሰው ደግሞ የአብርሃም ዘር ነውና ዛሬ መዳን ለዚህ ቤት ሆኖአል፤ የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።” ሰዎቹ ይህን በመስማት ላይ ሳሉ ኢየሱስ አንድ ምሳሌ ደግሞ ነገራቸው፤ እርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ ተቃረበ ሰዎቹ የእግዚአብሔር መንግሥት አሁኑኑ የምትገለጥ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የንጉሥነትን ሥልጣን ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር የሄደ አንድ መኰንን ነበረ፤ እርሱ ከመሄዱ በፊት ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ጠርቶ ለእያንዳንዱ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱ’ አላቸው። የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ስለ ነበር፥ ይህ ሰው በእኛ ላይ እንዲነግሥ አንፈልግም ሲሉ እርሱ ከሄደ በኋላ መልእክተኛ ላኩ። “ያ ሰው ንጉሥ ሆኖ በተመለሰ ጊዜ በተሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያኽል እንዳተረፉ ለማወቅ፥ ገንዘብ ሰጥቶአቸው የነበሩትን አገልጋዮቹን አስጠራቸው። የመጀመሪያው አገልጋይ ቀርቦ፦ ‘ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝ አንድ ምናን እነሆ፥ ዐሥር ምናን አትርፎአል’ አለው። ጌታውም ‘አንተ መልካም አገልጋይ! ደግ አደረግህ፤ በትንሽ ነገር ስለ ታመንህ እኔ ደግሞ በዐሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ’ አለው። ሁለተኛውም አገልጋይ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝ ምናን እነሆ! አምስት ምናን አትርፎአል’ አለው። ጌታውም ይህኛውን ‘አንተንም ደግሞ በአምስት ከተሞች ላይ ሾሜሃለሁ’ አለው። “ሌላውም አገልጋይ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ሆይ! የሰጠኸኝ ገንዘብ ይኸውልህ፤ በጨርቅ ቋጥሬ አስቀምጬው ነበር። ይህንንም ያደረግኹት አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፥ ያልዘራኸውንም የምትሰበስብ፥ ኀይለኛ ሰው መሆንህን ዐውቄ ስለ ፈራሁህ ነው’ አለው። ጌታውም ‘አንተ መጥፎ አገልጋይ! በአነጋገርህ እፈርድብሃለሁ፤ እኔ ያላስቀመጥኩትን የምወስድና ያልዘራሁትን የምሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆኔን ዐውቀሃል፤ ታዲያ ገንዘቤን ትርፍ በሚያስገኝልኝ በባንክ ለምን አላስቀመጥከውም ነበር? እኔ ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ እወስደው ነበር’ አለው። ከዚህ በኋላ ጌትዮው፥ በዚያ ቆመው የነበሩትን፦ ‘ምናኑን ከእርሱ ወስዳችሁ ዐሥር ምናን ላለው አገልጋይ ስጡት’ አላቸው። እነርሱም ‘ጌታ ሆይ! እርሱ እኮ ዐሥር ምናን አለው!’ አሉት። ጌትዮውም ‘ላለው ሁሉ ይበልጥ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል እላችኋለሁ። በእነርሱ ላይ እንድነግሥ ያልፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ግን እዚህ አምጥታችሁ በፊቴ ግደሉአቸው!’ ” አላቸው። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ጒዞውን ወደ ኢየሩሳሌም በመቀጠል፥ ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ፊት ይሄድ ነበር።

ሉቃስ 19:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወደ ኢያሪኮም ገብቶ በዚያ በኩል አልፎ እየሄደ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፤ ሀብታምም ነበረ። ኢየሱስ ማን እንደሆነም ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ አቃተው። በዚያችም መንገድ ማለፍ ነበረበትና ወደ ፊት ቀድሞ ሮጠና በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በቤትህ መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ፤” አለው። ፈጥኖም ወረደ፤ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው “ከኀጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ፤” ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን “ጌታ ሆይ! ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን መጥቶ አል፤ ምክንያቱም እርሱም የአብርሃም ልጅ ነውና፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና፤” አለው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሳለ፥ ወደ ኢየሩሳሌም በመቃረቡ፥ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ እንደሚገለጥ ይገምቱ ነበርና፥ ተጨማሪ ምሳሌ ነገራቸው። እንዲህም አላቸው “አንድ መኰንን ለራሱ የመንግሥትን ሥልጣን ተቀብሎ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ዐሥር አገልጋዮችንም ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘እስክመጣ ድረስ ነግዱ፤’ አላቸው። የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና ‘ይህ በላያችን እንዲነግሥ አንፈልግም፤’ ብለው በኋላው መልእክተኞችን ላኩ። መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን አግልጋዮች እንዲጠሩለት አዘዘ። የመጀመሪያውም ደርሶ ‘ጌታ ሆይ! ምናንህ ዐሥር ምናን አተረፈ፤’ አለው። እርሱም ‘መልካም፥ አንተ በጎ አገልጋይ፥ በጥቂት ነገር የታመንህ ስለ ሆንክ በዐሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ፤’ አለው። ሁለተኛውም መጥቶ ‘ጌታ ሆይ! ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ፤’ አለው። ይህናውንም ‘አንተንም በአምስት ከተማዎች ላይ ሾሜሃለው፤’ አለው። ሌላውኛውም መጥቶ ‘ጌታ ሆይ! በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንክ፤ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፤ ያልዘራኸውንም የምታጭድ ነህና፤’ አለው። እርሱም ‘አንተ ክፉ አገልጋይ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላስቀመጥኩትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደሆንሁ አወቅህ፤ ታዲያ ገንዘቤን ለገንዘብ ለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው ለምንድን ነው? እኔም መጥቼ ከነትርፉ እወስደው ነበር፤’ አለው። በዚያም ቆመው የነበሩትን ‘ምናኑን ውሰዱበት፤ ዐሥር ምናን ላለውም ስጡት፤’ አላቸው። እነርሱም ‘ጌታ ሆይ! ዐሥር ምናን አለው፤’ አሉት። ‘ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል እላችኋለሁ። ነገር ግን እነዚያን በላያቸው እንድነግሥ ያልፈለጉትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው፤ በፊቴም እረዱአቸው።’” ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር።