ሉቃስ 17:11-19
ሉቃስ 17:11-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ እዘንልን” አሉ። ባያቸውም ጊዜ፥ “ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ” አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ነጻ ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውየውም ሳምራዊ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ? ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?” እርሱንም፥ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው።
ሉቃስ 17:11-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኩል ዐለፈ፤ ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት። እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?” ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
ሉቃስ 17:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።
ሉቃስ 17:11-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ያልፍ ነበር፤ ወደ አንዲት መንደርም በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስም አያቸውና “ሂዱ! ሰውነታችሁን ለካህናት አሳዩ!” አላቸው፤ እነርሱም በመሄድ ላይ ሳሉ ከለምጻቸው ነጹ። ከእነርሱም አንዱ ከለምጹ መንጻቱን ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተመለሰ። ኢየሱስንም እያመሰገነ በእግሩ ሥር በግምባሩ ተደፋ፤ እርሱ የሰማርያ ሰው ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከለምጽ የነጹት ሰዎች ዐሥር አልነበሩምን? ታዲያ፥ ዘጠኙ የት አሉ? እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ሌላ አንድም አልተገኘምን?” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው፦ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
ሉቃስ 17:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ! መምህር ሆይ! ማረን፤” አሉ። አይቶም “ሂዱ፤ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ፤” አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያወደሰ ተመለሰ፤ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከሌላ ወገን ሰው በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም፤” አለ። እርሱንም “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው።