ሉቃስ 17:1-33
ሉቃስ 17:1-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፥ “መሰናክል ግድ ይመጣል፤ ነገር ግን መሰናክልን ለሚያመጣት ሰው ወዮለት። ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ አህያ የሚፈጭበት የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም በተሻለው ነበር። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወንድምህ አንተን ቢበድል ብቻህን ምከረው፤ ቢጸጸት ግን ይቅር በለው። በየቀኑ ሰባት ጊዜ ቢበድልም ሰባት ጊዜ ከተጸጸተ ይቅር በለው።” ሐዋርያትም ጌታን፥ “እምነትን ጨምርልን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ብትኖራችሁ ይህችን ሾላ ከሥርሽ ተነቅለሽ በባሕር ውስጥ ተተከዪ ብትሉአት ትታዘዝላችኋለች።” “አራሽ ወይም ከብት ጠባቂ አገልጋይ ያለው ከእናንተ ማን ነው? ከእርሻው በተመለሰ ጊዜ ጌታው ና፥ ፈጥነህ ወደዚህ ውጣና ከእኔ ጋር በማዕድ ተቀመጥ ይለዋልን? እራቴን አዘጋጅልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስም ታጥቀህ አሳልፍልኝ፤ ከዚህም በኋላ አንተ ብላ፥ ጠጣም ይለው የለምን? እንግዲህ ጌታው ያዘዘውን ሥራውን ቢሠራ ለዚያ አገልጋይ ምስጋና አለውን? እንዲሁ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ አድርጋችሁ ‘እኛ ሥራ ፈቶች አገልጋዮች ነን፤ ለመሥራትም የሚገባንን ሠራን’ በሉ።” ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ እዘንልን” አሉ። ባያቸውም ጊዜ፥ “ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ” አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ነጻ ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውየውም ሳምራዊ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ? ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?” እርሱንም፥ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው። ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም። እንኋት፥ በዚህ ናት፤ ወይም እነኋት፥ በዚያ ናት አይሉአትም፤ የእግዚአብሔር መንግሥትስ እነኋት፥ በመካከላችሁ ናት።” ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፥ “ከሰው ልጆች ቀኖች አንዲቱን ታዩ ዘንድ የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩአትም። እነሆ፥ በዚህ ነው፥ ወይም እነሆ፥ በዚያ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ ብልጭ ብሎ ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ እንደሚያበራ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ነውና። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ብዙ መከራን ይቀበላል፤ ይህች ትውልድም ትንቀዋለች፤ ትፈታተነዋለችም። በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡ ነበረ፤ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን አንድ አድርጎ አጠፋ። በሎጥ ዘመንም ሲበሉና ሲጠጡ፥ ቤት ሲሠሩና ተክል ሲተክሉ፥ ሲሸጡና ሲገዙ ነበረ። ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነመ፤ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ አይታወቅምም። ያንጊዜም በሰገነት ላይ ያለ፥ ገንዘቡም በምድር ቤት የሆነበት ሰው ለመውሰድ አይውረድ፤ በዱር ያለም ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት ዐስቡአት። ነፍሱን ሊያድናት የሚወድ ይጣላት፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚጥላትም ያድናታል።
ሉቃስ 17:1-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎችን የሚያሰናክል መምጣቱ አይቀርም፤ ነገር ግን ለመሰናክሉ መምጣት ምክንያት ለሚሆን ለዚያ ሰው ወዮለት። ይህ ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል፣ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። “ወንድምህ ቢበድል ገሥጸው፤ ቢጸጸት ይቅር በለው። በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና ሰባት ጊዜ፣ ‘ተጸጽቻለሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ ይቅር በለው።” ሐዋርያትም ጌታን፣ “እምነታችንን ጨምርልን” አሉት። ጌታም፣ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ሾላ፣ ‘ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ተተከል’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው። ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ዐራሽ ወይም በግ ጠባቂ የሆነ አገልጋይ ቢኖረው፣ ከዕርሻ የተመለሰውን አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ወደ ማእድ ቅረብ’ ይለዋልን? ከዚህ ይልቅ፣ ‘እራቴን እንድበላ አዘጋጅልኝ፣ እኔ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፤ ትጠጣለህ’ አይለውምን? እንግዲህ ይህ ሰው፣ አገልጋዩ የታዘዘውን በመፈጸሙ መልሶ ያመሰግነዋልን? ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቍጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ።’ ” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኩል ዐለፈ፤ ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት። እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?” ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤ ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።” ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም። ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤ ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል። “በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው። “በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው። “የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል። በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ፣ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ። ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል።
ሉቃስ 17:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው። በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ፦ ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው። ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ፦ ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም። እነርሱም፦ እነሆ በዚህ፥ ወይም፦ እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስቡአት። ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል።
ሉቃስ 17:1-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ሰዎችን አሰናክለው ወደ ኃጢአት የሚጥሉ ነገሮች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን የኃጢአትን መሰናክል ለሚያመጣው ለዚያ ሰው ወዮለት! ማንም ሰው ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ! ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው! በበደሉ ከተጸጸተም ይቅር በለው! በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና በቀን ሰባት ጊዜም ወደ አንተ እየመጣ ‘በበደሌ ተጸጽቼአለሁ’ ቢልህ ይቅር በለው።” ሐዋርያቱም ጌታ ኢየሱስን “እባክህ እምነት ጨምርልን” አሉት። ጌታ ኢየሱስም “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን የሾላ ዛፍ ‘ከዚህ ተነቅለህ በባሕር ውስጥ ተተከል!’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ አንዱ በእርሻ ሥራ የተሰማራ፥ ወይም በጎች የሚጠብቅ አገልጋይ ቢኖረው፥ አገልጋዩ ከሥራው በተመለሰ ጊዜ ወዲያውኑ ‘ና ተቀመጥና ራትህን ብላ’ ይለዋልን? ይልቅስ፥ ‘በል! ራቴን አዘጋጅልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣም አደግድገህ አገልግለኝ፤ ከዚህ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፥ ትጠጣለህ’ ይለው የለምን? ታዲያ፥ አገልጋዩ የታዘዘውን ስለ ፈጸመ ጌታው የሚያመሰግነው ይመስላችኋልን? እናንተም እንዲሁ የታዘዛችሁትን ሁሉ በፈጸማችሁ ጊዜ፥ ‘የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ የፈጸምነውም ግዳጃችንን ብቻ ነው’ በሉ።” ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ያልፍ ነበር፤ ወደ አንዲት መንደርም በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስም አያቸውና “ሂዱ! ሰውነታችሁን ለካህናት አሳዩ!” አላቸው፤ እነርሱም በመሄድ ላይ ሳሉ ከለምጻቸው ነጹ። ከእነርሱም አንዱ ከለምጹ መንጻቱን ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተመለሰ። ኢየሱስንም እያመሰገነ በእግሩ ሥር በግምባሩ ተደፋ፤ እርሱ የሰማርያ ሰው ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከለምጽ የነጹት ሰዎች ዐሥር አልነበሩምን? ታዲያ፥ ዘጠኙ የት አሉ? እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ሌላ አንድም አልተገኘምን?” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው፦ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ፈሪሳውያን ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ሲሉ ጠየቁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ሰዎች ነቅተው በሚጠባበቁት ዐይነት አይደለም፤ እንዲሁም ‘እነሆ፥ እዚህ ናት ወይም እዚያ ናት’ የምትባል አይደለችም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ነች።” ቀጥሎም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትናፍቁበት ቀን ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩም። ሰዎች ‘እነሆ፥ ክርስቶስ እዚህ ነው! ወይም እዚያ ነው!’ ይሉአችኋል፤ ነገር ግን አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በሰማይ ላይ ሲበርቅ ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ የሰው ልጅ በሚመጣበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አስቀድሞ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህ ትውልድም ሊናቅና ሊነቀፍ ግድ ነው። በኖኅ ዘመን እንደሆነው ዐይነት የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጥፋት ውሃ መጣና አጥለቅልቆ ሁሉንም አጠፋቸው። እንዲሁም ደግሞ በሎጥ ዘመን እንደሆነው ዐይነት ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲሸጡና ሲገዙ፥ አትክልት ሲተክሉና ቤትም ሲሠሩ ነበር። ነገር ግን ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው፤ የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል። “በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ፤ በእርሻም ቦታ ያለ ሰው ወደ ቤቱ አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ! ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ያድናታል።
ሉቃስ 17:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “መሰናክል የግዱን ሳይመጣ አይቀርም፤ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፤ ቢጸጸትም ይቅር በለው። በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ፥ በቀንም ሰባት ጊዜ ‘ተጸጸትሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው።” ሐዋርያትም ጌታን “እምነት ጨምርልን” አሉት። ጌታም አለ፦ “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል፤’ ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። “ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ አገልጋይ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ ‘ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ፤’ የሚለው ማን ነው? ‘የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ፤’ ይለው የለምን? ያዘዘውን ስላደረገ ያንን አገልጋይ ያመሰግነዋልን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ ‘የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል፤’ በሉ።” ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ! መምህር ሆይ! ማረን፤” አሉ። አይቶም “ሂዱ፤ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ፤” አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያወደሰ ተመለሰ፤ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከሌላ ወገን ሰው በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም፤” አለ። እርሱንም “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም ‘ይችትና!’ ወይም ‘ያቻትና!’ የምትባል አይደለችም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና፤” አላቸው። ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች መካከል አንዱን ለማየት የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ አታዩትምም። እነርሱም ‘እነሆ በዚህ’ ወይም ‘እነሆ በዚያ’ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ አንድ ስፍራ ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅም፥ በቀኑ፥ እንዲህ ይሆናል። አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህም ትውልድ ሊናቅ ይገባዋል። በኖኅ ዘመንም እንደሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመንም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፤ የጥፋት ውሃም መጣ፤ ሁሉንም አጠፋ። እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ፤ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፤ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱአት። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን የሚያጠፋ ሁሉ ይጠብቃታል።