ሉቃስ 16:10-13
ሉቃስ 16:10-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም። እንግዲህ፣ በዚህ ዓለም ሀብት ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውንማ ሀብት ማን ዐደራ ብሎ ይሰጣችኋል? በሌላው ሰው ሀብት ካልታመናችሁ፣ የራሳችሁ የሆነውን ሀብት ማን ይሰጣችኋል? “በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም ባሪያ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን ይጠጋል፤ ሌላውን ይንቃል። የእግዚአብሔርም የገንዘብም ባሪያ መሆን አትችሉም።”
ሉቃስ 16:10-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“በጥቂት የሚታመን በብዙ ይታመናል፤ በጥቂት የሚያምፅም በብዙም ቢሆን ያምፃል። በዐመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ በእውነተኛው ገንዘብ ማን ያምናችኋል? በሌላውስ ገንዘብ ካልታመናችሁ የራሱን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚችል አገልጋይ የለም፤ ካልሆነም አንዱን ይወድዳል፤ ሁለተኛውንም ይጠላል፤ ወይም ለአንዱ ይታዘዛል፤ ለሁለተኛውም እንቢ ይላል፤ እንዲሁም እናንተ ገንዘብ እየወደዳችሁ ለእግዚአብሔር መገዛት አትችሉም።”
ሉቃስ 16:10-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።
ሉቃስ 16:10-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በትንሽ ነገር የታመነ ሰው በትልቅ ነገርም የታመነ ይሆናል፤ በትንሽ ነገር የማይታመን ሰው ግን በትልቅ ነገርም አይታመንም። ታዲያ የዚህን ዓለም ሀብት በማስተዳደር የማትታመኑ ከሆናችሁ እውነተኛውን ሀብትማ ማን አምኖ ይሰጣችኋል? ደግሞም በሌላው ሰው ሀብት የማትታመኑ ከሆነ ለእናንተ የሚሆነውንስ ሀብት ማን ይሰጣችኋል? “አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌታ ማገልገል አይችልም፤ ይህ ከሆነ፥ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ አንዱን አክብሮ፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ ልትገዙ አትችሉም።”
ሉቃስ 16:10-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በትንሹ የታመነ በብዙም እንዲሁ የታመነ ነው፤ በትንሹ የሚያታልል በብዙም እንዲሁ ያታልላል። እንግዲያስ በዐመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አንድም አገልጋይ የለም፤ ወይ አንዱን ሲጠላ ሌላውን ይወዳል፤ ወይ አንዱን ሲጠጋ ሌላውን ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”